አገሩን ከመፈራረስ የታደገው አፍሪካዊ

108

ታዬ ለማ (ኢዜአ)

በኢትዮጵያ በተካሄደው 32ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ ላይ አንድ እንግዳ በአዲስ አበባ መዲና ተገኝቶ ነበር፡፡ ይህ ሰው በእግር ኳስ ተጫዋችነት ዝናው ከፍተኛ ቢሆንም ለአገሩ ሰዎች ግን እሱ እግር ኳስ ተጫዋች ብቻ እንዳልሆነ ይነገርለታል፡፡

“አገራችንን ከመፈራረስ ያዳነ” ከእግር ኳስ ተጫዋችም በላይ ሲሉ ይዘምሩለታል፤ የቀድሞ የቸልሲው ዝነኛ ተጫዋች ዴዴዬ ድሮግባ፡፡

የቴሌግራም ጋዜጠኛ አሌክሳንደር  አይስ ስለ አፍሪካዊ ድሮግባ ሲናገር በኮትዲቫር አቢጃን ያደረገው ጉዞ በጣም አስደናቂ እንደሆነ በመጥቀስ ነው፡፡

ዴዴዬ ድሮግባ በሀገሩ ዜጎች ዘንድ ከተጫዋችም በላይ እንደሆነ አይቻለሁ፤ ሰምቻለሁ ይላል፡፡

በኮትዲቫር አቢጃን ጎዳናዎች የድሮግባ ስም በተለየ ሁኔታ ይጠራል፡፡ በየቦታው የተሰቀሉት ባነሮች፣ ቢልቦርዶች አብዛኞቹ  የድሮግባን ምስሎች ይዘዋል በማለትም ይገልጻል፡፡ የማስታወቂያ ድርጅቶች እንኳን አብዛኛው ማስታወቂያቸውን የድሮግባን ምስል በመጠቀም ሲያስተዋወቁ ይታያል በማለት ጋዜጠኛው የተናገረው።

“ድሮግባ  ጎሎች ከማስቆጠሩ ብቻ እንዳይመስላችሁ  እንደዛ ካሰባችሁ ተሳስታችዋል” ያለው አይስ ይህ የሆነው አገሩን ከመፈራረስ እንድትድን ባደረገው ትልቅ አስተዋጾ  ነው ሲልም  ይናገራል ፡፡

የድሮግባ አገር አይቮሪኮስት፤ የዛሬዋ ኮትዲቫር እአአ  ከ2002 ጀምሮ በተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት ግጭት ለዜጎቿ ትልቅ የእልቂት ምክንያት መሆኑ የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው።

በአገሪቱ የተካሄደው ጦርነት እአአ እስከ 2006 ድረስ  በመንግስትና በአማጽያን ጎራ ተከፍላ ለአምስት አመታት የብጥብጥ ማዕከል ሆና ቆይታለች ፡፡

በአገሪቱ የነበረው የሁለቱ አካላት ፍጥጫ አገሪቱን በማፈራረስ ለህዝቡ እልቂት ምክንያት እንደሚሆን የተረዱት የተባበሩት መንግታትና ፈረንሳይ ጦራቸውን ይዘው ወደ ምእራባዊቷ አፍሪካ ኮትዲቫር እንዲገቡ  ምክንያት ሆኖል ፡፡

የተባበሩት መንግስታትም ሆነ ሌላው የፈረንሳይ ጦር በኮትዲቫር የተከሰተውን ግጭት ተኩስ ለማስቆም ወደ ኮትዲቫር ዘመናዊ መሳሪያውን ታጥቆ ቢገባም ያሰበውን ውጤት ግን ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ኮትዲቫርም የሰቆቃ መሬት መሆኗ እየባሰ መጣ እንጂ ምንም ሊሻሻል አልቻለም፡፡

አቢጃን የተወለደውና እንደ ማንኛውም ልጅ በመሬቷ ቦርቆ ያደገው ድሮግባ የአገሩ እንዲህ መሆን ክፉኛ ከሚያሳስባቸው  ሰዎች መካከል ነበር፡፡

ምንም እንኳን ኑሮውን በአውሮፓ ቢያደርግም አገሩ ለመፈራረስ መቃረቧ የእግር እሳት ሆኖበት ስለነበር እንዴት አድርጎ  ለአገሩ እንደሚደርስላት ሲያወጣ ሲያወርድ መቆየቱን ድሮግባ  ለቴሌግራም ጋዘጠኛ ተናግሯል፡፡

ይህ  ሃብታምና ዝነኛው እግር ኳስ ተጫዋች፤ እግር ኳስን እንዴት ለአገሩ ሰላም ማዋል እንዳለበት  ወቅቱን መጠበቅ ጀመረ።

አገሩ ለአለም ዋንጫ ለማለፍ የነበረባትን የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታ ለማድረግ ወደ ሱዳን አመራች፡፡ ድሮግባም ከቡድኑ አንደኛው አባል ነበርና ከቡድኑ አባላቱ ጋር ወደ ሱዳን አመራ፡፡

ኮትዲቫር እአአ በ2006 ያደረገችውን ጨዋታ በማሸነፍ በታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ ለአለም ዋንጫ አለፈች፡፡ በጦርነት በግጭት በሰዎች ሞት መካከል ኮትዲቫር በደስታ ጮቤ ሰከረች፡፡

ተቃዋሚውም ሆነ መንግስት አገራቸው ለአለም ዋንጫ በማለፏ ምሽቱን እንኳን ደስ አላችሁ ሲባባሉ አመሹ።  

አገራቸውን ለአለም ዋንጫ ማሳለፍ ቢችሉም የአገራቸው መፈራረስ  ደስታቸውን  ሙሉ እንዳላደረገው የተናገረው ድሮግባ የጨዋታውን ማለቅ ተከትሎ አንድ ያልታሰበ ነገር አደረገ፡፡

የወቅቱ የኮትዲቫር ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የሆነው ድሮግባ አገሩ  ለአለም ዋንጫ ማለፏን ተከትሎ በብሄራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያው ሁለቱ አንታረቅም፤ እንተላለቃለን ያሉትን ፓርቲዎች ወደ አንድነት እንዲመጡ ጥሪ አቀረበ፡፡

በጉልበቱ  ተንበረክኮ "እናንተ   ከሰሜን፣ ከምስራቅ፣ ከደቡብ፣ ከመካከለኛው፣ ከምእራብ የምትገኙ የአገሬ ልጆች አንድ  ነገር ልንገራችሁ፡፡  እኛ የአይቮሪኮስታውያንን አላማ በመጋራት፤ በጋራ በመጫወት ፣ ማሸነፍ እንደሚቻል በማሳየት   ገድል መስራት  እንደምንችል አሳይተናል።" ሲል ተናገረ፡፡

ቀጥሎም "የዛሬው ውጤታችን እናንተን ከማስደሰት አልፎ ኮትዲቫር  አንድ እንድትሆኑ ያደርጋታል ብለን  ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እባካችሁ ሁላችሁም ከልብ ይቅር ተባባሉ፡፡” ሲል ተማጽኖውን አቀረበ፡፡

“ኮትዲቫር ይህ አይገባትም፡፡ እባካችሁ ሁላችሁም  መሳሪያችሁን ጣሉ፡፡ ተኩሳችሁን አቁሙ፡፡  ምርጫ አካሂዱ፤ በምርጫ ተሸናነፉ፡፡  ሁሉም ነገር ለኮትዲቫር መልካም ይሁን” ሲል ተንበርክኮ በቴሌቭዥን ፕሮግራሙ አማጽያኑንና መንግስትን ተማጸነ፡፡

“ሁሉም ነገር ለኮትዲቫር መልካም ይሁን” ሲል ተንበርክኮ ለአገሩ መልካም ምኞቱን ገለጸ።

እግር ኳስን ተጠቅሞ ለሁለቱ ፓርቲዎች ጥሪ ያቀረበው ድሮግባ ጥሪው ተሰማና ኮቲዲቫርን ለመበተን የተቃረቡት ፓርቲዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ማድረጉን በዘገባው ተመላክቷል።

ድሮግባ ታሪክን ቀየረ፡፡ እግር ኳስ የፈጠረችለትን ዝናና ተወዳጅነትን  ተጠቅሞ  ተኩሶች በኮትዲቫር እንዳይሰሙ አደረገ ሲልም በወቅቱ አልጄዚራ ሰፊ ሰገባ አስነብቦ ነበር፡፡

እነ ዩናይትድ ኔሽን ያልቻሉትን፤ የፈረንሳይ ጦር ያልመለሰውን የኮትዲቫር ግጭትን የድሮግባ የሰላም ጥሪ የአማጽያኑንም ሆነ የመንግስትን ልብ ማሸነፍ ቻለ፡፡

ዴዴ ድሮግባ  የተናገረው የደቂቃ ንግግር መንግስትንም ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያሳመነ ነበር፡፡  ከሱ ንግግር በኋላ ሁለቱም አካላት ተኩስ ላለመተኮስ ተስማሙ፡፡  ወዲያውኑ ያቋረጡትን የሰላም ውይይት ዳግም እንደጀመሩም ቴሌግራም በዘገባው አስነበበ ፡፡

የድሮግባን መልዕክት ተከትሎ  የቢቢሲ መረጃ እንደሚያስነብበው  እአአ በ2007 ሁለቱ አካላት የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ። ፕሬዘዳንት ፓግቦም በኮትዲቫር ጦርነት እንዳበቃ አወጁ፡፡

ድሮግባ በዚህ አላበቃም፤ የመንግስት አመራሮችና የአማጽያኑ መሪ የበለጠ እንዲቀራረቡ አገሪቱ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለባትን ውድድር የአማጽያኑ ግዛት አካባቢ ጨዋታው እንዲደረግ አደረገ፡፡

በወቅቱም የሁለቱ መሪዎች የአገሪቱን ሰንደቅ አላማ በጋር ቆመው እንዲሰቅሉ በማድረግ የአገሪቱ ሰላም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ሚናውን ተወጣ።

ድሮግባ ለቴሌግራም ጋዜጠኛ የሁኔታውን  አስደናቂነት እንዲህ ነበር ያለው "እስቲ አስበው ሁለት  የተጣሉ  የአንድ አገር  ሰዎች አጠገብ ለአጠገብ ቆመው የአገራቸውን ሰንደቅ አላማ በጋራ ሲሰቅሉ ስታይ ከዚህ በላይ ምን የሚያስደስት ነገር አለ"።  

አሁን አይቮሪኮስት ዳግም የተወለደች ያህል ተሰምቶኛል ሲልም ተናግሯል።

ኮትዲቫርያውያንም ዛሬም ድረስ ለአገሩ ሰላም የተጫወተውን ሚና፤ ያለውን የአገር ፍቅር በማስታወስ እጅጉን ይወዱታል። ዛሬም ጀግናቸው እንደሆነ በአደባባይ  እየመሰከሩለት ነው።

የአፍሪካን ኮከብ ሁለት ግዜ ማሸነፍ የቻለው የቀድሞ የማርሴና  የቸልሲ ተጫዋች ድሮግባ እግር ኳስን ቢያቆምም የአፍሪካ ሰላም ከአገሩ አልፎ የአፍሪካን ልማት፣ የአፍሪካን ጤና ጉዳዩ በማድረግ እንቅስቃሴውን በማጠናከር ላይ ይገኛል፡፡

ይህ አፍርካዊ ጀግና በጤናው ዘርፍ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ከአፍሪካ፤ ከአውሮፓ መሪዎች ጋር በአፍሪካ ጉዳይ ላይ በመወያየት የአገሩን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ችግር ለመቅረፍ እየሰራ ይገኛል፡፡

በቅርቡም ለ32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ ለመካፈል ወደ ኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ መምጣቱ ይታወሳል፡፡

በአፍሪካ ቢዝነስ ጤና ፎረም ላይ በመገኘት ስለ አፍሪካ ጤና ተወያይቷል። በቀጣይም የአጉሪቷ ጤናና ትምህርት ላይ እንደሚሰራም በዚሁ መድረክ አረጋግጧል፡፡

አገራችንን የረገጠው ድሮግባ እግር ኳስ የፈጠረለችለትን ዝነኝነት በመጠቀም አገሩን ከመፍረስ አድኗል። ለዚህም ነው ተጫዋቹ  ከእግር ኳስ ተጫዋች በላይ  የሚዘመርለት፡፡

እኛ የኢትዮጵያ ልጆች ከዚህ ምን እንማር ይሆን፡፡ ዝነኝነትን፣ ታዋቂነትን በመጠቀም አገርን በማዳን፣ በመርዳትና በማገዝ የአገራችን ዝነኛ ሰዎችስ ምን እየሰራን ይሆን? ከድሮግባ ተሞክሮስ ምን ተምረን ይሆን? መልሱን ለሁላችንም ልተወው። ቸር እንሰንብት!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም