የካላዛር መድኃኒትን የጎንዮሽ ጉዳት የሚቀንስና የሕክምና ጊዜውን የሚያሳጥር ምርምር እየተካሄደ ነው

63

ጎንደር የካቲት 9/2011 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካላዛር መድኃኒትን የጎንዮሽ ጉዳት የሚቀንስና የሕክምና ጊዜውን የሚያሳጥር ምርምር እያካሄድኩ ነው አለ።

ሆስፒታሉ ከዚህ ቀደም ባደረገው ምርምር ሁለት ወራት የሚፈጀውን የሕክምና አሰራር ወደ 17 ቀናት ዝቅ አድርጓል፡፡

የሆስፒታሉ የካላዛር ሕክምናና ምርምር ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር እርዝቃ መሐመድ ለኢዜአ እንዳስረዱት የምርምሩ ዋና ዓላማ መድኃኒቱ በበሽተኞች ኩላሊት፣ ጉበትና ጣፊያ ላይ የሚያደርሰውን የጎንዮሽ ጉዳት መቀነስና የሕክምና ጊዜውንም ማሳጠር ነው።

ማዕከሉ ለሁለተኛ ጊዜ በሚያደርገው ምርምር ሕክምናውን ከ17 ወደ 13 ቀናት ለማሳጠር ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል።

እንዲሁም ለበሽታው ተጠቂዎች በቀን ሁለት ጊዜ የሚሰጠውን መርፌ ወደ አንድ ዝቅ ለማድረግ እንደሚሰራ አስተባባሪዋ አስረድተዋል፡፡

ማዕከሉ መድኃኒቱን በ21 ፈቃደኛ ታማሚዎች ላይ በመሞከር ውጤታማነቱን እንደሚገመግም አስታውቀዋል።

ምርምሩ በቀጣይ ሁለት ዓመታት እንደተጠናቀቀ በዓለም ጤና ድርጅትና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሚሰጠው ማረጋገጫ  ወደ ትግበራ እንደሚሸጋገር ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ ምርምሩን የሚያከናውነው በሽታውን ለመቆጣጠር ከሚሰሩ አጋር ድርጅቶች በሚያገኘው የገንዘብና የሕክምና መሣሪያዎች ድጋፍ መሆኑንም ዶክተር እርዝቃ ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ ከአምስት ዓመታት በፊት ባደረገው ምርምር የበሽታው ተጠቂዎችን ለማከም ይፈጅ የነበረውን የሁለት ወራት ጊዜ ወደ 17 ቀናት ያሳጠረ መድኃኒት ሥራ ላይ አውሎ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

በማዕከሉ ሕክምናቸውን የሚከታተሉት አቶ ይሁኔ ተዋቸው ሕክምናውን ከጀመሩ ወዲህ በጤናቸው ላይ ለውጥ እየታየ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ሌላው ታማሚ አቶ ወንድሙ መንገሻ የበሽታውን ምንነት ባለማወቅ ለረጅም ጊዜ ተገቢውን ሕክምና ሳያገኙ መቆየታቸውን ገልጸዋል።በሽታው እንዳለባቸው በምርመራ ሲረጋገጥ ሕክምናውን እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ 27 የህሙማን አልጋዎች ያሉት ሲሆን፤በየዓመቱ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ሕሙማን ነጻ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የካላዛር በሽታ ''ሳንድ ፍላ'' በምትባል ዝንብ መሳይ ነፍሳት ንክሻ የሚከሰት ሲሆን፣ ነፍሳቷ በአሸዋማ ቦታ፣ በቀይ የግራር ዛፍና በኩይሳ አፈር ውስጥ ሰፊ የመራባት ዕድል አላት፡፡

ቆላማና ሞቃታማ የአየር ንብረት ባለባቸው አካባቢዎች የበሽታው ስርጭት ተስፋፍቶ የሚገኝ ሲሆን፣ በአማራ ክልል በማዕከላዊ፣ በምዕራባዊና በደቡብ ጎንደር ዞኖች አካባቢዎች በስፋት ይስተዋላል፡፡

በሽታው የታማሚዎችን ቆሽት በማጥቃት የጤና ችግር ያስከትላል። በፊትና በአፍንጫ ላይ የሚወጣ ቁስልም የበሽታው ዋነኛ ምልክቶች ናቸው፡፡በፍጥነት ካልታከሙት የሞት አደጋን ያስከትላል ይላሉ በሽታውን በማስመልከት የተዘጋጁ መረጃዎች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም