ኢትዮጵያ የደመቀችበት የህብረቱ ጉባኤ

58


በሀብታሙ አክሊሉ (ኢዜአ)

"አስተማማኝ መፍትሄ በአስገዳጅ ሁኔታ ለሚፈናቀሉ አፍሪካዊያን ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች" በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ የቆየው 32ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ተጠናቆ የሃገራቱ መሪዎች ወደየሃገራቸው ተመልሰዋል። ጉባኤው በበርካታ ጉዳዮቹ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ጉባኤዎች የተለየ ሆኖ አልፏል። ለህብረቱ መመስረት ባለውለታ ለሆኑት አፄ ሃይለስላሴ የመታሰቢያ ሃውልት እንዲሰራ ከማድረግ ግብፅን ከበርካታ አመታት በኋላ የህብረቱ ሊቀመንበር አድርጎ እስከ መምረጥ የመሳሰሉ የተለዩ ጉዳዮች በጉባኤው ታይተዋል።

ሃገራችንም ጉባኤው ያመጣላትን ሲሳይ እንዲሁ በዋዛ አላሳለፈችውም። ፈርጀ ብዙ የጎንዮሽ ውይይቶችን ከተለያዩ ሃገራት መሪዎችና አለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች ጋር ከውናበታለች። በኢንዱስትሪው ዘርፍም ያላትን ተሞክሮ ለሌሎች እዩልኝ ከማለት አልፋ የኢንዱስትሪ ፓርኳን ለጉብኝት በመፍቀድ ተሞክሮዋን አጋርታለች። በዚህም አድናቆትን አትርፋበታለች።

በህብረቱ ጉባኤ ከተከወኑ አያሌ ተግባራት ውስጥ ለአብነት ያህል የመረጥናቸውን ጉዳዮችን  እንመልከት።

የመታሰቢያ ሃውልት ለቀድሞ ባለውለታ

የአፍሪካ ህብረት የቀድሞ ስያሜውን የ‘አፍሪካ አንድነት ድርጅት’ ይዞ በ1955 ዓ.ም በ32 ሃገራት እንዲመሰረት ከፍተኛ ድርሻ ለነበራቸው ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ የመታሰቢያ ሃውልት በቅጥር ግቢው እንዲቆምላቸው ማድረጉ በመሪዎቹ ጉባኤ ከተከወኑ ተግባራት የመጀመሪያውን ቦታ ይይዛል።

የህብረቱ መሪዎች ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ለህብረቱ መመስረት ላደረጉት አስተዋፅኦ የመታሰቢያ ሃውልት እንዲቆምላቸው እኤአ በ2017 ዓ.ም ባሳለፉት ውሳኔ መሰረት ሃውልቱ መቆሙና በ32ኛው የህብረቱ ጉባኤ ወቅትም ሃውልቱ ሊገለጥ መቻሉን ከሰሞኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ከተሰራጩ መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።

አፄ ሃይለስላሴ ለአፍሪካ ነፃነት ብሎም ለአህጉሪቱ ጠንካራ አንድነት ከቀድሞ አፍሪካውያን መሪዎች ጋር በመሆን የህብረቱ መመስረት እውን እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ለማድረጋቸው የሃውልቱ መቆም ምስክር ሊሆን እንደሚችል በሃውልት ምርቃቱ ወቅት ተገልጿል።   

በሃውልት ምርቃቱ ስነስርኣት ወቅትም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድና የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማህማት፣ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ የጋናው ፕሬዚዳንት አኩፎ አዶ፣ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ እና ሌሎች የአፍሪካ ሃራት መሪዎች ተገኝተዋል።

የስርአተ ፆታ ሽልማት ለሃገራችን

በህብረቱ ጉባኤ ከተከናወኑ አበይት ጉዳዮች ሌላው ሃገራችን ‘የአፍሪካ ህብረትን የ2018 የስርአተ ፆታ ሽልማት’ ያገኘችበት መሆኑ ይጠቀሳል። ሽልማቱንም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ተቀብለዋል።

ሽልማቱን አስመልክተው የወጡ መረጃዎች እንደጠቆሙት የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንትን ላስተዋወቀች፣ ግማሽ የካቢኔ ሃላፊነትን ለሴቶች ለሰጠች፣ ወሳኝ የሃገሪቱ የስልጣን ቦታዎች በሴቶች እንዲያዙ ላደረገች ሃገር ሽልማቱ የሚያንስ እንጂ የሚበዛ አይደለም።

በተጨማሪም በታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የመከላከያ ሚኒስትር ሃላፊነት ለኢንጂነር አይሻ መሃመድ የሰጠች እንዲሁም በሃገሪቷ ቀደምት የሚኒስትር መስሪያ ቤት የሆነውን የሰላም ሚኒስቴር ስልጣንን ለሙፈሪያት ካሚል ጀባ ላለች ሃገር የስርኣተ ፆታው ሽልማት የሚያስደንቅ ሊሆን እንደማይችል ነው ዘገባዎች ያስረዱት።

የስርአተ ፆታ ሽልማቱን የአፍሪካ ህብረት ከመንግስታቱ ድርጅት ምጣኔ ሃብት ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት እንደሸለሙም ዘገባዎቹ አክለዋል።

የግብፅ የህብረቱ መሪ ሆና መመረጥ

የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አል ሲሲ ለአንድ አመት የሚቆየውን የአፍሪካ ህብረት የሊቀመንበርነት ሃላፊነት ከሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ተቀብለዋል። 32ኛውን የህብረቱ ጉባኤ የተለዩ ከሚያደርጉት ጉዳዮችም አንዱ ይኸው ግብፅ ፊቷን ወደ አፍሪካ መመለሷን በተግባር ያረጋገጠችበት የሃላፊነት ሹመት ነው።

እኤአ በ1995 ዓ.ም በህብረቱ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በመጡት ያኔ በነበሩት መሪዋ ሆስኒ ሙባረክ ላይ ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ በኋላ ነው ግብፅ በአፍሪካ ላይ አኩርፋ የቆየችው። ሆኖም ለአሁኑ ፕሬዚዳንቷ ምስጋና ይግባቸውና ኩርፊያውን ወደ ጎን ትተው ወደ አህጉሪቱ ፊታቸውን መልሰዋል። አሁን ደግሞ ለአንድ አመትም ቢሆን ህብረቱን በሊቀመንበርነት የመምራት ዕድሉን ሃገራቸው እንድታገኝ አድርገዋል።

ፕሬዚዳንት አል-ሲሲም  የአፍሪካን ሰላምና ደህንነት በተጠናከረ መሰረት ላይ ለመገንባት የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ ለጉባኤ ተሳታፊዎች ተናግረዋል። አዲሱ የህብረቱ ሊቀመንበር በመቀጠልም ሽብርተኝነትን በፋይናንስም ሆነ የትግሉን ውስብስብነት ከግንዛቤ በማስገባት በህብረት ለማጥፋት ከመረባረብ ውጪ አማራጭ እንደሌለ ተናግረዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2002 ከተመረጡት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ታቦ ኢምቤኪ አንስቶ 17 መሪዎች የህብረቱ ሊቀ-መንበር ሆነዋል።

የሃገራችን የኢንዱስትሪ ልማት ተሞክሮ

የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የቦሌ ለሚ የኢንዱስትሪ ፓርክን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸው ወቅትም ዚምባቡዌ መሰል የኢንዱስትሪ ልማት ለማካሄድ ከኢትዮጵያ ተሞክሮ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በፕሬዚዳንቱ የሚመራው የልዑካን ቡድንም ኢትዮዽያ የኢንዱስትሪ መንደሮችን በመገንባት የውጭ ኢንቨስተሮችን ከመሳቧም በላይ ለዜጎቿ ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠሯን ስፍራው ላይ በመገኘት አረጋግጠዋል።

ዚምባቡዌም በተመሳሳይ ሂደት ልዩ የምጣኔ ሃብት ዞን እያቋቋመች መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ዚምባቡዌም ፓርኮቹን ገንብታ የውጭ ኢንቨስተሮችን ትጋብዛለች ብለዋል። የ6 አመታትን ዕድሜ ብቻ የቆጠረው የኢትዮዽያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ትግበራ በርካታ የህንድም ሆነ ሌሎች ሃገራት ኩባንያዎችን ወደ ሃገሪቱ እንዲመጡ እንዳደረገ መገንዘባቸውንም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል።


ፕሬዚዳንቱ የጎበኙት ጄይ ጄይ የተሰኘው የጨርቃጨርቅ ኩባንያ ብቻውን ለ4ሺ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን እና በአጠቃላይ በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ተመሳሳይ ፋብሪካዎች ባለፉት አምስት አመታት ብቻ ለ45ሺ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል መፍጠራቸውን መገንዘባቸውን አንስተዋል።

 “…ዚምባቡዌም መሰል አይን ከፋች የኢንዱስትሪ ዞኖችን በማቋቋም ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ለወጣት ሴቶች እና ልጃገረዶች የስራ ዕድል መፍጠር ትፈልጋለች። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ስራ ከመፍጠር ባሻገር ቴክኖሎጂን ብሎም የተለያዩ የስራ ክህሎቶችን ያመጣሉ። ዚምባቡዌም ለመከተል የምትፈልገው ይህንኑ መንገድ ነው። …” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

ውጤታማ የጎንዮሽ ውይይት

ሃገራችን ጉባኤው በተሳካና ባማረ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የተለያዩ ተግባራትን ከማከናወን ባለፈ ከመጡ እንግዶች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውጤታማ ምክክር አድርጋለች። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከጉባኤው ተሳትፎ ውጪ እረፍት አልባ ቀናትን ያሳለፉት  ከአህጉራዊና አለም አቀፍ እንግዶቻቸው ጋር በመወያየት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ከሱዳን እና ከግብፅ አቻዎቻቸው ጋር ያደረጉት የሶስትዮሽ ውይይት ውጤታማነትን መገናኛ ብዙሃን በሰፊው ዘግበውታል። መሪዎቹም በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ማናቸውንም አይነት እንቅፋቶችን ማለፍ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ከህብረቱ ጉባኤ ጎን ለጎን በተከናወነው ምክክራቸው የሶስቱ ሃገራት መሪዎች ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከፍተኛ ፖለቲካዊ መፍትሄን ሊሰጥ የሚችል ውሳኔ ላይ ለመድረስ እንደሚፈልጉ አፅንኦት ሰጥተው ተወያይተዋል።

በሌላም በኩል ኢትዮጵያና ሱዳን በጋራ የድንበር ቁጥጥርን ማጠናከር ዙሪያም ምክክር ያካሄዱት ከህብረቱ ጉባኤ ጎን ለጎን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ሃገራቱ የነበራቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል።

ምንም እንኳ አዲስ አበባና ካርቱም የተጠናከረ የሁለትዮሽ ግንኙነት ቢኖራቸውም በሃገራቱ ድንበር አከባቢ ከህገወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር መረጋጋት የማይታይበት ሁኔታን ለመቀየር የሚያስችል ውይይት አካሄደዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ  ከሶማሊያው ፕሬዝዳን መሃመድ ፋርማጆ፣ ከጋናው ፕሬዝዳንት ናና አኩፎና ከቦትስዋና ፕሬዝዳንት ሞክግዌሲ ማሲሲ፣ ከቱንዝያው ፕሬዝዳንት ቤጂ ካይድ ኢሴብሲ፣ ከጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማርጌሌ፣ ከሞሮኮው ጠቅላይ ሚንስትር ሳአዴዲን ኦቶማን፣ ከአልጄሪያው ጠቅላይ ሚንስትር አህመድ ኦያህያ እና ከጊኒው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴ ጋርም የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።

የኢስቶኒያው ፕሬዝዳንት ክርስቲ ካልጁይድ፣ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲሁም የአወሮፓ ህብረት ኮሚሽን የውጭ ጉዳይና ደህንነት ፖሊሲ ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ፌደሪካ ሞግሪኒ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ካካሄዱት ባለስልጣናት ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም