በከተሞች ማህበረሰባዊ መስተጋብሩን አቀናጅቶ መምራት ካልተቻለ የነዋሪን ፍላጎት ማሟላት ፈታኝ ያደርገዋል - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

98

አዲስ አበባ  የካቲት 9/2011 በከተሞች አካባቢ ማህበረሰባዊ መስተጋብሩን አቀናጅቶ የመምራት ችግርን በመፍታት የነዋሪን ፍላጎት ያማከለ አቅርቦት ማመጣጠን ካልተቻለ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቷ በጅግጅጋ ከተማ ተገኝተው 'መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና' በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ያለውን 8ኛውን የከተሞች ፎረም በይፋ አስጀምረዋል።

በጂግጂጋ ከተማ የታደሙ ከተሞች የሚያቀርቡትን ኤግዚቢሽን ፕሬዚዳንቷ መርቀው ከፍተዋል።

አሁን ለኤግዚቢሽን የተዘጋጀው ስፍራ በቀጣይ ለወጣቶች አረንጓዴ መዝናኛ ስፍራ ሆኖ እንዲያገለግልም የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በከተሞች አካባቢ ያለውን ችግር በመፍታት ከተሞችን ለነዋሪው ምቹ ለማድረገ መስራት ተገቢ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

በመክፈቻ ንግግራቸው እስካሁን ሲካሄዱ የቆዩት የከተሞች ፎረም በመልካም አስተዳደር የተገኙ ለውጦች ለህብረተሰቡ ይፋ የተደረጉባቸው እንደነበሩ ፕሬዚዳንቷ አስታውሰዋል።

በየከተሞቹ ሰዎች በመንገድ ዳር ወድቀው ባሉበትና የአገልግሎት አሰጣጥ ባልተስተካከለበት የለማ ከተማ መፍጠር እንደማይቻል ገልጸው ይህንን ችግር ለመፍታት መትጋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

''ስለዚህ ስራዎችን በፍጥነትና በጥራት መፈፀም በጣም የሚያስፈልግበት ወቅትና በጋራ ሆነን ለእድገታችን መስራት የሚገባን ወቅት ነው'' ብለዋል።

''የከተሞችን እድገት ለማረጋገጥ በአንድነት መስራት ያስፈልጋል'' ያሉት ፕሬዚዳንቷ በኢትዮጵያ የሚካሄደው የከተሞች ፎረም የመልካም አስተዳደር ውጤት ለህዝቡ የሚተዋወቅበትና የህብረሰተሰቡ ተሳትፎ የሚረጋገጥበት መሆኑን ገልጸዋል።

አገራዊ መግባባትን በመፍጠርም ለጋራ ልማት መረጋገጥ ውጤት እንዲያመጣ ታስቦ ፎረሙ እንዲከበር መደረጉንም አስታውቀዋል።

ፎረሙ በከተሞች መካከል በጎ የሆነ ውድድር እንዲኖር በማድረግ ውጤታማ ለሆኑት እውቅና እየተሰጠ የመጣበት አውድ እንደሆነም ገልፀዋል።

የከተሞችን ልማትና ሰላም ለማረጋገጥ ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

8ኛው የከተሞች ፎረም ለተከታታይ ስድስት ቀናት በፓናል ውይይቶችና ኤግዚቢሽኖች የሚከበር ሲሆን ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ዕውቅናና ሽልማት ይሰጣል።

በከተሞች ፎረም ከተሞች የተሻለ ተሞክሮአቸውን ይዘው የሚቀርቡበት በመሆኑ እርስ በርስ ለመማር ከፍተኛ ዕድል የሚፈጥር አጋጣሚ እንደሆነ ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም