በኦሮሚያ የተሽከርካሪ አደጋን ለመቀነስ ህብረተሰብ አቀፍ ጥረት እየተደረገ ነው

52

አዳማ የካቲት 8/2011 በኦሮሚያ ክልል አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የተሽከርካሪ አደጋን ለመቀነስ ህብረተሰብ አቀፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ትራንስፖርት ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ በትራፊክ ደህንነት ዙሪያ በመጀመሪያው ግማሽ የበጀት ዓመት የተከናወኑ  ስራዎችን ለመገምገም ለሁለት ቀናት ያዘጋጀው መድረክ በአዳማ ከተማ  እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ  መክፈቻ ስነስርዓት ወቅት በባለስልጣኑ የትራፊክ ደህንነት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ተመስገን እንዳሉት በግማሽ የበጀት ዓመቱ በክልሉ 2 ሺህ 349 የተሽከርካሪ አደጋዎች ደርሰዋል።  

በዚህም  852 ዜጎች ህይወታቸውን እንዳጡና  በሌሎች ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንዲሁም 253 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙንም ጠቅሰዋል፡፡

ይህም አደጋው አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከመሆኑ የተነሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የክልሉን መልካም ገጽታ በማጉደፍ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

አደጋው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በሞትና በአካል ላይ የደረሰው ጉዳት ቢቀንስም በንብረት ላይ ግን ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቁመዋል።

አደጋውን ለመቀነስ እንዲቻል ባለፉት ስድስት ወራት ለ1 ሚሊዮን 700ሺህ የክልሉ ህብረተሰብ  በትራፊክ ደህንነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት በባለቤትነት ስሜት እንዲንቀሳቀስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የተሽከርካሪ አደጋ በህብረተሰቡና በሌሎችም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር መከላከል የሚያግዝ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡  

በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ደህንነትና ስራ ሂደት ባለቤት ኮማንደር ንጉሴ ግርማ በበኩላቸው የተሽከርካሪ  አደጋን ለመከላከል ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ቢከናወንም የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጠት እንደሚቀር ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ጉዳቱን ለመቀነስ በግማሽ የበጀት ዓመቱ ህብረተሰቡንና ሌሎችንም አካላት በማስተባበር ባገኘው አንድ ሚሊዮን 600ሺህ ብር ድጋፍ ያዘጋጃቸው የትራፊክ ምልክቶች  አደጋ በሚበዛባቸው አካባቢዎች  መትከሉን አመልክተዋል።

በዚህ ወቅት የትራፊክ ህግና ደንብ በመተላለፍ 124 ሺህ አሽከርካሪዎች ተከሰው ከ69 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲቀጡ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ኮማንደር ንጉሴ ገለፃ ህግን ከማስከበር ይልቅ የግል ጥቅማቸውን በሚያሳድዱና የሥነ ምግባር ችግር ባለባቸው  የትራፊክ ፖሊስ አባላት ላይ የእርምት እርምጃ እየተወሰደ ነው።

እየተባባሰ በመጠው የተሽከርካሪ አደጋ  በሰዎች ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ረታ በላቸው ናቸው።

የአሽከርካሪዎች ጉድለት፣የመንገድ ዲዛይንና የተሽከርካሪ ቴክኒክ ችግር ለአደጋው መከሰት ምክትል ኮሚሽነሩ በምክንያትነት  ከጠቀሷቸው መካከል ይገኙበታል፡፡

እነዚህን  ችግሮች ከመሠረቱ ለመፍታት የባለድርሻ አካላት ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም