የተደረገላቸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማህበራዊና የጤና ችግራቸውን እንዳቃለለላቸው ተጠቃሚዎች ተናገሩ

58

የካቲት 8/2011 በአዲስ አበባ በእድሜ የደከሙና  በቂ የገቢ ምንጭ  የሌላቸው ግለሰቦች በበጋ በጎ ፍቃደኞች የተደረገላቸው ድጋፍ  የማህበራዊና ጤና ችግራቸውን እንዳቃለለላቸው ተጠቃሚዎች  ገለጹ።  

የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌደሬሽን ጽህፈት በበኩሉ የበጋ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለሀገር እድገት ከፍተኛ ድርሻ ቢኖረውም ስራውን በተፈለገው ደረጃ መምራት አልተቻለም ይላል፡፡

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከተሰጣቸው መካከል  በባለቤታቸው ጡረታ የሚተዳደሩት የአዋሬ አካባቢ ነዋሪ  ወይዘሮ ብዙነሽ ወልደ ጻዲቅ አንዷ ናቸው።

የሚረዳቸው ዘመድና ገንዘብ ስለሌላቸው ባረጀና በፈራረሰ የቀበሌ ቤት ውስጥ በመኖራቸው ብርድና ዝናብ  በመፈራረቁ ለበሽታ መጋለጣቸውን ይናገራሉ።

 “ችግሬን ያዩ የአካባቢው ነዋሪዎች ቤቴን በማደሳቸው ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፤ ለረዱኝም ሰዎች ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ይባርክልኝ፤ ሀገራችንንም ሰላም ያድርገው” በማለት የተደረገላቸውን ድጋፍ በምርቃትና  በደስታ ጭምር የገለፁት።

የካዛንቺስ አካባቢ ነዋሪ  ወይዘሮ አለሚቱ ሞላው አርባ አምስት አመታት የኖሩባት የቀበሌ ቤት  በእርጅና ምክንያት ጣሪያው ማፍሰሱና የመጸዳጃ  ቤት ፍሳሽ ቤታቸው ውስጥ በመግባቱ ከጤና ችግርም ባለፈ  ጎረቤት እንኳን ገብቶ ሊጠይቃቸው እንዳልቻለ  ይናገራሉ።

“በትዳር በኖርኩበት ግዜ ልጆች ባይኖሩኝም ያሳደኳቸው የዘመድ ልጆች በእርጅና ግዜዬ አልጠየቁኝም” ነው ያሉት።

ችግራቸውን ያዩ የአካባቢው ወጣቶችና የቀበሌ አስተዳደሩ የህክምና ወጪያቸውን በመሸፈን፤ ቤታቸውን ማደሳቸውን የተናገሩት ወይዘሮ አለሚቱ የአረጋውያን ማህበርም ለእለት ቀለባቸው ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል።   

አቶ ወንደወሰን ሽፋ የትራፊክ እንቅስቃሴን በማሳለጥ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በበጎ ፍቃደኝነት ይሰራሉ።

“ሰዎች ባላቸው አቅም መልካም  ነገርን ካበረከቱ ሀገራችንን መለወጥ እንችላለን” በሚል እምነት  ላለፉት አምስት አመታት  በበጎፈቃድ ማገልገላቸውንም ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በየወሩ በሚያደርጉት የቤተዘመድ ጉባኤ  አቅም የሌላቸው ሰዎች ቤት በመገኘት ከሚያዋጡት አነስተኛ ገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ነው ያስረዱት።

ላለፉት አራት አመታት ደም  በመለገስ የህሊና እርካታ ማግኘቱን የተናገረው  ወጣት ዘመን አለሙ ደግሞ ምንም እንኳ ወጣቶች ገንዘብ ባይኖራቸውም እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን  በማዋጣት፤ ለበጎ አድራጊዎች ደብዳቤ በመጻጻፍ ያረጁ የሆስፒታል አልጋዎችን አስጠግነው ለገጠር ህክምና ተቋማት እየሰጡ መሆኑን ተናግሯል ፡፡

በደም ጠብታ ክበብ በመሳተፍም በቋሚነት ደም በመለገስ ለሌሎች አርአያ ለመሆን  ከብሄራዊ ደም ባንክ ጋር  በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

በበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 58ሺ500 ሰዎች በማሳተፍ መንግስት ዘርፉን ለመተግበር ሊያወጣ የነበረውን 25 ሚሊዮን ብር ለማስቀረት ወደ ተግባር መገባቱን   የሚገልጹት    የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌደሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት አብረሀም ይርጋ ናቸው ፡፡ በሂደቱም ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 24 ሺ111 በጎ ፍቃደኞች ሆነዋል።  

እንደ ሃላፊው ገለፃ የክረምት የበጎ ፍቃድ ሥራን በበጋውም ለማስቀጠል በተደረገው ጥረት ባለፈው አመት የነበረውን 24ሺህ 500 ተሳታፊዎች  ቁጥር በዚህ አመት ወደ 58ሺህ 500 ለማሳደግ መሰራቱን አስረድተዋል ፡፡

በከተማዋ  ከንቲባና በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የተጀመረው የአረጋውያን ቤት የመጠገንና የመረዳዳት ባህልን ለማጎልበት በተደረገው ጥረት በበጋው ወራት 30 ቤቶች ታድሰዋል ፡፡

የበጋ ወራት የበጎ ፈቃድ ተሳታፊዎች ቁጥር ከክረምቱ መቀነሱን መሆኑን የተናገሩት ሃላፊው፤ ለተሳታፊዎች እውቅናና ማበረታቻ አለመሰጠት፣ የህብረተሰቡ የግንዛቤ አለማደግ፣  እንዲሁም የሚመራበት የህግ ማእቀፍም  ያለመኖሩን እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል። 

በክረምት ወራት በርካታ ተማሪዎች እረፍት መሆናቸውና በተለይ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች   ወቅታዊ በመሆናቸው ለበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ቁጥር መቀነስ ተጨማሪ ምክንያት መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ 

በከተማዋ ባለፈው ክረምት በተሰራው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንድ ሚሊዮን ሰዎችን ለማሳተፍ ታቅዶ ስምንት መቶ ሺ ሰዎች በማሳተፍ 55 ሚሊዮን ብር የመንግስትን ወጪ ማዳን መቻሉን ከአዲስ አበባ ወጣቶች ፌደሬሽን የጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም