በምስራቅ ወለጋ ዞን የተስተጓጎለውን የፍትህ አገልግሎት ሥራ ለማስተካከል እየተሰራ ነው

36

ክልል የካቲት 8/2011 በአካባቢው በነበረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ተስተጓጉሎ የነበረውን የፍትህ አገልግሎት ሥራ ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን የምስራቅ ወለጋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለጸ፡፡

ባለጉዳዮች በበኩላቸው በችግሩ ምክንያት ፍርድ ቤቶች በመዘጋታቸው አጋጥሟቸው የነበረው መጉላላት በአሁኑ ወቅት እየቀነሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ተወካይ አቶ አለሙ ጉታ እንዳሉት የፍትሀብሔርና የወንጀል ጉዳዮችን ጨምሮ ባለፉት ስድስት ወራት ከቀረቡት 10ሺህ 726 መዝገቦች ውስጥ 8ሺህ 995 የሚሆኑት ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ከዕቅዱ አንጻር አፈጻጸሙ  እንደሚያንስ  አመልክተው  ወደ ኋላ የቀረውም  በአካባቢው ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት መሆኑንና በቀጣይ ለማካካስ ተጨማሪ ረዳት ዳኞችን ከወረዳዎች በማስመጣት ስራውን ለማቀላጠፍ  እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ አለሙ እንዳሉት ሰላም ለማስፈን የህግ የበላይነት መከበርና ለዚህም ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል፡፡

በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የዳኝነት አገልግሎት የስራ ሂደት መሪ አቶ ፍቃዱ መኩሪያ በበኩላቸው በሰላም መታወክ ምክንያት ፍርድ ቤቱ ከ20 ቀናት በላይ በመዘጋቱ የስራ አፈጻጸማቸው መቀነሱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደተረጋጋ ሥራ በመገባቱ ባለጉዳዮች ሳይጉላሉ ወደ ኋላ የቀሩትን መዝገቦችን ለይቶ ለማይትና የባከነውን ጊዜ ለማካካስ እየተረባረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

"በአካባቢው ተከስቶ በነበረው ችግር ምክንያት በተወሰነ ደረጃ ለዘገዩ መዝገቦች ቅድሚያ በመስጠት እየተሰራ ነው" ያሉት ደግሞ በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የእቅድ፣ በጀትና ሪፎርም የሥራ ሂደት መሪ አቶ ጫላ ሴጎ ናቸው፡፡

የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንዳርጌ ገመዳ በበኩላቸው ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በሰላም ጉዳይ ተከታታይ ውይይት በማድረግ አካባቢውን ማረጋጋት በመቻሉ የግልም ሆነ  የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ ስራ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ አንዳርጌ እንዳሉት በተለይ ወደ ኋላ የቀሩ የመንግስት ሥራዎችን ለማስተካከል ከፈጻሚ አካላት ጋር በደረሱት ስምምነት መሰረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

ባለጉዳዮች በበኩላቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ምክንያት ፍርድ ቤቶች በመዘጋታቸው አጋጥሟቸው የነበረው መጉላላት በአሁኑ ወቅት እየተቃለለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

አቶ ከፈለው ጋሩምሳ በዞኑ ሊቃ ዱለቻ ወረዳ የጃርሶ ባንቢች ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ አሁን በአካባቢ  ሠላም በመስፈኑ  በችግሩ ምክንያት የዘገየባቸውን የፍርድ ቤት ጉዳይ ለማስፈጸም  ነቀምቴ ወደ ሚገኘው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

ወደፍርድ ቤቱ ከመጡ በኋላ መጉላላት ሳይገጥማቸው በአግባቡ እየተሰተናገዱ መሆኑን ጠቅሰው ሰላምን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ሁሉ እንደ ሀገር ሽማግሌ በመሳተፍ የድርሻቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ ጫሊ ተመስገን በበኩላቸው ቀደም ሲል መንገድ በመዘጋት ምክንያት ከወረዳቸው ሲመጡ ፍርድ ቤት የነበራቸው ቀጠሮ ተስተጓጉሎባቸው እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

አሁን በአካባቢው አንጸራዊ ሰላም በመስፈኑ ያለባቸውን የፍርድ ቤት ክርክር መቀጠላቸውን ነው የገለጹት፡፡

 “ አሁን የተሻለ ነው፣ ሁሉም በሰላም ወጥቶ ወደ ስራው ይሰማራል፤ በሰላምም ወደቤቱ ይመለሳል “ ያሉት አቶ ጫሊ የአካባቢው ሰላሙ መልሶ እንዳይስተጓጎል መንግስትና ህዝብ ተቀራርበው በቅንጀት እንዲሰሩ አመልክተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም