የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ እየደረሰበት ካለው ውድመት ለመታደግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቆመ

178

ባህርዳር የካቲት 8/2011 የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ እየደረሰበት ካለው ውድመት ለመታደግ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ አሳሰቡ።

ፓርኩን ከአደጋ ለመታደግ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የምክር መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

ዶክተር ደሳለኝ በእዚህ ወቅት እንዳሉት ህገወጥ አደን፣ ሰደድ እሳት፣ የደን ውድመት፣ ህገወጥ ሰፈራ፣ ልቅ ግጦሽና ህገወጥ የአሣ ማስገር ስራ በፓርኩ ላይ የተደቀኑ አደጋዎች ናቸው።

ለፓርኩ ጥበቃ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን፣ የመንገድ መሰረተ ልማት አለመስፋፋት፣ የፓርኩ ሠራተኞች ቁጥር ማነስና ለዱር እንስሳት በቂ ጥበቃ አለማድረግ ለችግሩ መባባስ ምክንያቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ከናይጄርያ የመጡ ፈላታዎች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ እንስሳትን ይዘው በፓርኩ ውስጥ መኖራቸውና ህገወጥ ሰፈራ ሌሎች የችግሩ ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት በፓርኩ እየደረሰ ባለው አደጋ የተለያዩ ጥንታዊ የደን ዝርያዎችና ብዝሃ ህይወቶች፣ ጎሽ፣ ዝሆንና ጥቁር ጋማ ያለው የአፍሪካ አምበሳ በመጥፋት ላይ ናቸው።

ፓርኩን ከተጋረጠበት አደጋ ለማዳን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ህብረተሰብና ለሌሎች ባለርሻ አካላት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ስለፓርኩ ጠቀሜታ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

በፓርኩ ውስጥ በሚገኙ የዱር እንስሳት፣ እፅዋትና ደኖች እንዲሁም በአሳ ሃብት ልማት ላይ ያተኮረ ጥናት በዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች  እተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።

ብሄራዊ ፓርኩን ከተደቀነበት አደጋ በዘላቂነት ለመታደግ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በበኩላቸው ህገወጥ አደን፣ ደን ጭፍጨፋ፣ ወራሪ መጤ አረሞች የፓርኩ የስጋት ምንጭ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ውጭ የመጡ ተንቀሳቃሽ ከብት አርቢዎች በፓርኩ ላይ የሚያደርሱትን አደጋ በዘላቂነት ለመፍታት ከሱዳን መንግስት ጋር በመነጋገር ጉዳት ያደረሱ ፈላታዎች ከአካባቢው እንዲወጡ በጋራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

የአካባቢ ደንና አየር ንበረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ በበኩላቸው የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ዘላቂ ካልሆነ የሃብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ በፓርኩ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን በቅንጅት መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ከተደቀነበት አደጋ ለመታደግ ሁሉም አካል በባለቤትነት ሊሰራ እንደሚገባ አስረድተዋል።

የአልጣሽ ፓርክን ለቱሩዝም ልማት ለማዋልና የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲሟላ የክልሉ ምክር ቤት የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እንደሚያከናውን አስታውቀዋል።

የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ከ2 ሺህ 665 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት ያለው ነው።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ ላይም ፓርኩን የተመለከቱ የተለያዩ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ምሁራና ሌሎች አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም