የመርካቶ አውቶቡስ ተርሚናል ግንባታ 46 በመቶ ደርሷል

69

አዲስ አበባ የካቲት 8/2011 የመርካቶ አውቶቡስ ተርሚናል ግንባታ 46 በመቶ መድረሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ የእግረኛና ብዙሃን ትራንስፖርት አስተዳደር ኃላፊ አቶ ናትናኤል ጫላ እንዳሉት በመርካቶ የተሳፋሪዎችን ምቾት ጠብቆ በርካታ አገልግሎቶችን በአንዴ መስጠት የሚያስችል ዘመናዊ ተርሚናል በ200 ሚሊዮን ብር እየተገነባ ነው።

ግንባታውን በ2011 በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዶ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑንና አፈጻጸሙ 46 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

20 አውቶቡሶችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግደው ተርሚናሉ የራሳቸው መግቢያና መውጫ ያላቸው ሁለት ወለሎች፣ የአስተዳደር ቢሮዎች፣ የአውቶቡስ መጠበቂያ ቦታ፣ የትኬት መሸጫ፣ የተሳፋሪ መጫኛና ማራገፊያ ስፍራዎችን ያካተተ ነው።

ከ50-80 ሺህ የመርካቶ ገበያተኛችን የትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል ታስቦ የሚገነባው ተርሚናሉ በ4 ሺህ 125 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን በሠዓት ለ6 ሺህ የብዙሃን ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች አገልግሎት ይሰጣል። 

ከተማ አስተዳደሩ አሮጌ ተርሚናሎችን ዓለም በደረሰበት ደረጃ ማሻሻል፣ የማስተናገድ አቅማቸውን ማሳደግና ማልማት ስራ በመከወን ላይ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ የመርካቶ ተርሚናል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠው ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም እንደነበረ አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም