የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ሥራው ለእርሻ ሥራችን ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል....የምዕራብ ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች

242

አምቦ የካቲት8/2011 በአካባቢያቸው የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ሥራዎች ለእርሻ ሥራቸው ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን በምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ከ545 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች የተሳተፉበት የተፋሰስ ልማት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን አስታውቋል።

በዞኑ ባኮ ወረዳ የጉዲና ወልቅጤ ቀበሌ አርሶ አደር ሚሊኪ ጭምዴሳ እንዳሉት ላለፉት ስድስት ዓመታት በቀበሌያቸው በተካሄደው የተፋሰስ ልማት ሥራ በተነሳሽነት ሲሳተፉ ቆይተዋል።

ይህም የእንስሳት ልቅ ግጦሽን ከማስቀረት ባለፈ ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖች እንዲጠበቁ ማድረጉን ነው የገለጹት።

" በተለይ የተጎሳቆሉ ተፋሰሶች መልሰው መልማታቸው የእርሻ መሬታቸው በጎርፍ እንዳይጋለጥና ለምነቱ እንዲጨምር አድርጓል " ብለዋል

ለምነቱ እየተሻሻለ በመጣው የእርሻ መሬታቸው  ላይ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት በዓመት ከምርት ሽያጭ እስከ 40 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

"አውቀንም ይሁን ሳናውቅ የተፈጥሮ ሃብታችንን ማውደማችን ጎድቶናል"  ያሉት ደግሞ የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቆሪቾ ዶዮ ናቸው።

እሳቸውን ጨምሮ የቀበሌው ማህበረሰብ ከዚህ  ድርጊት በመታቀብ ለተከታታይ ዓመታት ባከናወኑት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በተጨባጭ ለውጥ በመታየቱ ዘንድሮም ልማቱን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በአንድ ሄክታር ማሳቸው ላይ በሰሩት የድንጋይ እርከን የመሬት ለምነቱ መሻሻሉን የገለጹት ሌላኛው የቀበሌው  አርሶ አደር ቶልቻ በዳዳ ናቸው ። 

በእዚሁ መሬት ላይ በቅርቡ ከሰበሰቡት የመኽር እርሻ የተሻለ የገብስና የስንዴ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የእርከን ሥራ በተሰራባቸው ተፋሰሶች ላይ የመኖ ዝርያ  በማልማት በበጋ ወራት የነበረባቸውን የግጦሽ እጥረት ማቃለል እንደቻሉ የተናገሩት ደግሞ በሊበን ጃዊ ወረዳ ሮጌ ዳኒሳ ቀበሌ አርሶ አደር ፊጡማ  ለታ ናቸው፡፡

የምዕራብ ሸዋ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ ደበሎ በበኩላቸው የዘንድሮ ተፋሰስ ልማት ከጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በ22 የገጠር ወረዳዎች በመካሄድ  ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ከአንድ ወር በላይ በሚቆየው በእዚሁ የልማት እንቅስቃሴ ከ545 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ የተጎሳቆለ 156 ሺህ 456 ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም