በአለርት ሆስፒታል የተገልጋዮች ቁጥርና አገልግሎቱ የተጣጣመ አይደለም ተባለ

62

አዲስ አበባ የካቲት 8/2011 በአዲስ አበባ የሚገኘው አለርት ሆስፒታል የተገልጋዮች ቁጥርና የአገልግሎት መሰረተ ልማቱ ተመጣጣኝ እንዳልሆኑለት አስታወቀ።

'የልዕልት ዘነበወርቅ ሃኪም ቤት' በሚል ይታወቅ የነበረው የዛሬው አለርት ሆስፒታል ከዓመታት በፊት ትኩረቱን በስጋ ደዌ ህሙማን ማከሚያና ማገገሚያነት አድርጎ ነበር የተቋቋመው።

አሁን ላይ ግን የድንገተኛ አደጋን፣ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምናንና የጨቅላ ህጻናትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ14 በላይ ዘርፈ ብዙ የቀዶ ህክምና አገልግሎቶችን ይሰጣል።

ባለፉት ስድስት ወራትም 219 ሺህ  ህሙማን በሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት አግኝተዋል።

ሆስፒታሉ የግማሽ ዓመት ስራ አፈጻፀሙን ዛሬ ከህዝብ ክንፍ ጋር በመገመገመበት ወቅት እንደተገለጸው ግን፤ የሆስፒታሉ ተገልጋይ ቁጥር በየጊዜው እያሻቀበ መጥቷል።

ሆኖም አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችና ቁሳቁሶች ሊሟሉለት ባለመቻሉ ሁሉንም ህሙማን በሚገባው መጠን ማገልገል ተስኖታል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ይሄይስ ፈለቀ እንደተናገሩት በአንድ ዓመት ከ400 ሺህ በላይ ተገልጋዮችን ያስተናግዳል፤ ባለፉት ስድስት ወራትም 219 ሺህ በላይ ህሙማን ህክምና አግኝተዋል።

በህብረተሰቡ በኩል የህክምና አገልግሎት ግንዛቤ በመዳበሩ የተገልጋዮች ቁጥር በመናሩ የመድሃኒት፣ አልጋና የህክምና መሳሪያዎች በሆስፒታሉ ተገልጋዮች በኩል የሚነሱ ዋነኛ የቅሬታ ምንጮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ተቋሙ ሰፊ ግቢ ቢኖረውም ለአገልግሎት የሚውሉ ግንባታዎች ህንጻ ባለመኖራቸው የህክምና ክፍሎች ጥበት እንዳለም ተናግረዋል።

ሆሰፒታሉ ችግሩን ለመፍታት የተለያየ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፣ ከነዚህም ውስጥ ሆስፒታሉ አገልግሎት በአራት እጥፍ የሚጨመርና በኢትዮጵያ ትልቁን የድንገተኛ አደጋ ህክምና ማዕከል የሚሆን ባለ 8 ፎቅ ህንጻ በሶስት ዓመት ውስጥ ይገነባል ብለዋል።

ለስጋ ደዌ ህሙማንን ቅድሚያ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸው፤ የህሙማኑን ወረፋና መጉላላት ለመቀነስም የራሱ ህንጻ ሊገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

በግንባታ ላይ የሚገኙት የአስተዳድር፣ ጨቅላ ህጻናት፣ የክትባትና መጸዳጃ ቤት ግንባታዎችም በአምስት ወራት ተጠናቀው አገልግሎት ይሰጣሉ ብለዋል።

ማዕከሉ ከውጭ የሚገቡ የህክምና መሳሪያዎችን ለማሟላት የግዥ ስርዓቱ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስለሚከናወን የግዥ አፈጻጽም ሂደቱ በፍጥነት ለማከናወን አለመቻሉን ዶክተር ይሄይስ አብራርተዋል። 

ችግሮችን በጊዜያዊነት ለመቀርፍ የቀዶ ህክምና ክፍሎችን መጨመር፣ ከጤና ጣቢያዎች ትስስር በማድረግ ሪፈራል መቀነስ፣ ማታና በበዓል ቀናት አገልግሎት ተጨማሪ ሰዓት አገልግሎት በመስጠት የሆስፒታሉን ጫና ለመቀነስና ተገልጋዮች ፈጣን ህክምና እንዲያገኙ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም