የአዋሽ ወንዝን በአግባቡ መጠቀምና መገምገም የሚያስችል ሠነድ ይፋ ሆነ

59

አዲስ አበባ  የካቲት 8/2011 በሕንዱ የሳይንስና የአካባቢ ጥበቃ ማዕከል የተዘጋጀው የአዋሽ ወንዝን በአግባቡ መጠቀምና መገምገም የሚያስችል ሠነድ ይፋ ሆነ።

ሠነዱ የህንድና የኢትዮጵያ የዘርፉ ምሁራን በወንዙ ላይ ለሁለት ዓመታት ባደረጉት ጥናትና ምርምር መዘጋጀቱ ተገልጿል።

በዋነናት በአዋሽ ወንዝ የሚካሄደውን የውኃ ጥራት ቁጥጥር ሥርዓት ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የልኬት ቀመሮችም አሉት።  

በማዕከሉ ጥናቱን የመሩት ኩማር ያጋይ እንደተናገሩት ወንዙን በተመለከተ ከዘርፉ ምሁራንና ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር ሰፊ ምክክር ተደርጓል።

መረጃዎች ለማሰባሰብ በቀጥታ የአዋሽ ወንዝን ተንተርሰው ከሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር የገጽ ለገጽ ውይይትና ቃለ መጠይቅ መካሄዱንም አስረድተዋል።

የአዋሽ ወንዝን በተመለከተ ቀደም ሲል በዘርፉ ምሁራን የተጻፉ መጽሃፎችና የተለያዩ ጥራዞችን በማጣቀሻነት መጠቀሙንም ነው የገለጹት።

ሠነዱ ኅብረተሰቡ የአዋሽ ወንዝን ለመጠቀም በምን መልኩ የውኃ ጥራቱን መጠበቅ እንደሚገባ እንዲገነዘብ መረጃ በማቀበል አበርክቶው ጉልህ መሆኑን አውስተዋል። 

በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአካባቢ ብክለት ቁጥጥርና ክትትል ዳይሬክተር ሙሉ ብርሃን ታሪኩ እንዳሉት ሠነዱ አዋሽን ለመገምገም መለኪያ ቀመር ያቀርባል።

ይህም ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ አገልግሎት የሚሰጠውን የአዋሽ ወንዝ ጥራትና ንጽህና ለመጠበቅ እንዲሁም ወንዙን በአግባቡ ለመጠቀም ወሳኝ መሆኑን ነው ያነሱት።

ከጊንጪ የሚነሳው የአዋሽ ወንዝ ኦሮሚያን፣ አፋርን፣ አማራን፣ ሶማሌና ደቡብ ክልሎችን እንዲሁም አዲስ አበባና ድሬዳዋን ሠንጥቆ የሚያልፍ ረጅም ወንዝ ነው።

አዋሽ ወንዝ 12 ሺ 500 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን 112 ሺህ ኪሎ ሜትር ስኩዬር መሬትም ይሸፍናል። በመጨረሻም በምስራቅ ኢትዮጵያ ከአገር ሳይወጣ በረሃ ውስጥ ያበቃል።

አዋሽ ወንዝ ለቆቃ፣ ለአዋሽ ሁለትና ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፤ ለተንዳሆና ለቀሰም የመስኖ ልማት እንዲሁም ለበርካታ ሰዎችና ከብቶች የመጠጥ ውኃ ሆኖም እያገለገለ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም