ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ለሚገነቡ ትምህርት ቤቶች የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

115

አዲስ አበባ የካቲት 8/2011 ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ለሚገነቡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የተፈራረሙት ከክልሎቹ የትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች ጋር ሲሆን ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ 20 ሚሊዮን ብር ተመድቧል።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ማስፋትን እንደ አንድ የስራ አቅጣጫ በመያዝ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ተገልጷል።

ለዜጎች ጥራት ያለው ትምህርት በፍትሃዊነት ማዳረስ ትውልድን ለማነጽ የሚያግዝ ቁልፍ ተግባር መሆኑንም ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ  ተናግረዋል።

በተለይ በገጠር በርቀት ምክንያት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ምጣኔ ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አክለዋል።

በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች 20 ሚሊዮን ብር ተመድቦላቸው የሚገነቡት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም በክልሎቹ ረጅም ርቀት ተጉዘው የሚማሩ ተማሪዎችን እንግልት እንደሚቀንስ አውስተዋል።

የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ቶማስ የማሎና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ቶማስ ኩዊ የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ በክልሎቻቸው የትምህርት ተደራሽነትን በማሳደግ ተማሪዎች በአቅራቢያቸው እንዲማሩ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ አመቺ ቦታ ከተመረጠ በኋላ የመሰረት ድንጋይ እንደሚቀመጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኢዜአ  አስታውቋል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ቀደም ሲልም በአማራ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች ለሚገነቡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል። 

በተጨማሪ ከተለያዩ ተቋማት ያሰባሰቧቸውን የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችም በደቡብ ክልል ሀድያ ዞን ሾኔ ከተማ ለሚገኘው ሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አስረክበዋል።

የህጻናት አልጋዎች፣ ማቀዝቀዣዎች፣ ተሽከርካሪ ወንበሮችና የህክምና መመርመሪያ መሳሪያዎች ነው ለሆስፒታሉ ያስረከቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም