የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበርና ተመድ የአየር ብክለትን ለመከላከል የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

77
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2010 የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበርና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የከባቢ አየር ተቋም የአየር ብክለትን በጋራ ለመከላከል የሚያስችላቸውን የአምስት ዓመት የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ። ትናንት የተፈረመው ስምምነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 1ሺህ የሚሆኑ የአትሌቲክስ የመወዳደሪያ ቦታዎችን የሚያስተሳስር የአየር ጥራት መቆጣጠሪያ ስርአት የመፍጠር ዋንኛ አላማ አለው። የአየር ንብረትና ንጹህ አየር ጥምረት በመወዳዳሪያ ቦታዎች የአየር ጥራት መቆጣጠሪያ ስርአትን እንደሚዘረጋ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል። በስምምነቱ አማካኝነትም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በመሮጫ ቦታዎቹ ትክክለኛና የተቀናጀ ዓለም አቀፍ የአየር ጥራት የመረጃ ቋት እንደሚኖር ተጠቁሟል። ፕሮፌሽናል አትሌቶች ክልላዊና ብሔራዊ መንግስታት፣ የማህበረሰብ መሪዎችና በአጠቃላይ የስፖርቱ አፍቃሪ ጥራቱን በጠበቀ አየር በመሮጥ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ስምምነቱ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ጥራት እንዲጠበቅ እየተደረጉ ያሉ ቅስቀሳዎችም በስምምነቱ አማካኝነት ይታገዛሉ ተብሏል። የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ 'ከተመድ የከባቢ አየር ተቋም ጋር መስራታችን እጅግ የሚያስደስት ነው' ብለዋል። በአየር ብክለት ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥና የአየር ጥራት መረጃ በመሰብሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአትሌቶችና የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ጤና ለመጠበቅና የአየር ብክለትን ለመከላከል እንደሚያግዝ ተናግረዋል። መንግስታት፣ የማህበረሰብ መሪዎችና አጠቃላይ ህብረተሰቡ ለሚተነፍሱት እያንዳንዱ አየር ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የተመድ የከባቢ አየር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ኤሪክ ሶልሄይም በበኩላቸው 'የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በአየር ጥራት ዙሪያ የፈረመው ስምምነት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የወሰደው ከፍተኛ የሆነ እርምጃ ነው' ብለዋል። አየር ቢበከል ሁሉም ተጎጂ እንደሆነና በስምምነቱ አማካኝነት ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ መሮጫዎች ላይ የአየር ጥራት መቆጣጠሪያ መተከሉ ለስፖርቱ ጤናማነት የተወሰደ መልካም እርምጃ እንደሆነም ተናግረዋል። 'ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮና ከሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴና ሌሎች ታላላቅ ከሆኑት የቀድሞ አትሌቶች በጉዳዩ ዙሪያ የሚያስፈልገውን ድጋፍ በማግኘታችን በዓለም ላይ ያለውን አየር በእርግጠኝነት ንጹህ ማድረግ እንችላለን' ብለዋል። ከ500 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሯጮች የአየር ብክለት በጤና ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ በተመለከተ በአምስት ዓመቱ የስምምነት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመዞር ግንዛቤ እንደሚያስጨብጡ ተጠቅሷል። በተጨማሪም የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የጤናና የስራ ክፍል 'የአየር ንብረትና የአትሌቶች ብቃት ያላቸው ትስስር' በሚል ጥናት እንደሚያካሄድ አስታውቋል። የፌዴሬሽኖች ማህበሩ በሚያካሂዳቸው ውድድሮችና መርሃግብሮች አገልግሎት ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮች እንዲቀነሱ የሚወሰደው እርምጃ የየአገራቱ ፌዴሬሽኖች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስቧል። በሚያዚያ ወር 2010 ዓ.ም መጨረሻ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበርና የተመድ የከባቢ አየር ተቋም "ብሪዝ ላይፍ" የሚባል ንቅናቄ ይፋ ያደረጉ ሲሆን ኢትዮጵያዊው ሻለቃ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴና እንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ የንቅናቄው በአምባሳደርነት መመረጣቸው የሚታወስ ነው። በየዓመቱ በአየር ብክለት ምክንያት 7 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚሞቱ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የገለጸ ሲሆን ጤና ድርጅቱ ባስቀመጠው የአየር ጥራት ደረጃ መመሪያ የዓለማችን 91 በመቶ የሚጠጋ ህዝብ ንጽህና ያለው አየር እንደማይተነፍስ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም