ታሪካዊና ባህላዊ አሻራዎች ያረፉበት የወለጋ ሙዚየም

184

የካቲት 7/2011  የወለጋ ሙዚየም በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኝ ሲሆን  በውስጡ ተደራጅተው ያሉት  ቅርሶች ትኩረትን የሚሰቡ ናቸው፡፡

በ1975 የተመሰረተው ሙዚየሙ  ከ1 ሺህ 700 በላይ ቅርሶች ይገኙበታል።

አቶ ሙላቱ ከበደ የምስራቅ ወለጋ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት  የባህል ተቋማት ስራ ሂደት መሪ ሲሆኑ፣  ሙዚየሙ የያዛቸው የኢትዮጵያውያን በተለይም የኦሮሞ ሕዝብ ታሪካዊና  ባህላዊ  ቅርሶችን ጠብቆ ለማቆየት ጥረት እየተደረገ መሆኑን  ይናገራሉ፡፡

በሙዚየሙ የሕዝቡን  አኗኗር ፣ ታሪክ ፣፣አለባበስ፣የስልጣኔና ዕደ ጥበባዊ ቅርሶች፣ የተለያዩ የዱር አራዊት ቅሪተ አካላት በውስጡ አካቶ ይዟል፡፡

በተለይ  የአገራቸውን ክብር ለማስጠበቅ የተዋደቁትን የእነአብዲሳ አጋን ታሪክ የያዘና መግቢያው በር ላይ በኢትዮ -ኢጣሊያ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች መትተው የጣሉት የወራሪው ኃይል ሄሊኮፕተር ሞተር ቅሪት አካል ይታያል፡፡

በነቀምቴ ከተማ መሃል የሚገኘው ሙዚየም ባህላዊ ቅርሶችን፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን ፣ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብቶችን የሚያመለክት መረጃዎች አካቷል፡፡ 

የዝሆን ጥርስን ጨምሮ የእንስሳት ቅሪተ አካላት፣ ረጅም ዕድሜ ያላቸው የመገልገያ  ቁሳቁስ በሙዚየሙ ይታያሉ፡፡

ሙዚየሙ  ፊት ለፊቱ " W " እና ከኋላው ደግሞ  " M " የሚሉ  የእንግሊዘኛ ፊደሎች ቅርፅ ይዞ   "ወለጋ ሙዚየም" የሚለውን ቃል እንደሚወክል ነው የስራ ሂደቱ  መሪ ያመለከቱት፡፡

እነዚህን ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች በድረ ገጽና በሌሎችም የመገናኛ ዘዴዎች በማስተዋወቅ በየዓመቱ እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች እንደሚመለከቱት አቶ ሙላቱ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

የሕዝቡን ባህላዊና ታሪካዊ አሸራ ያረፉበት የሙዚየሙ ቅርሶች ተጠብቀው ለትውልድ ለማቆየት እንዲያግዝ በቅርቡ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከፌዴራል የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመተባበር መዚየሙ እንዲጠገን ተደርጓል፡፡

በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋት ተቀዛቅዞ የነበረው ጉብኝት እየተሻሻለ በመምጣቱ የማስተዋወቁ ሥራ መቀጠሉን የተናገሩት አቶ ሙላቱ፣  ሳቢነት ባለው አደረጃጀት ተዘጋጅቶ ትውልዱ ታሪኩን እንዲረዳና እንዲጠብቀው በመሰራት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ዋናው ከገቢው ሳይሆን የአባቶች ቅርስ ታውቆ እንዲጠበቁና ሁሉም መጥቶ ቢጎበኘው እውቀትና ግንዛቤ ሊያገኝበት ይችላል ብለዋል፡፡

የነቀምቴ ከተማ ነዋሪው  አባት ጡረተኛ መምህር አብዲሳ ጉደታ ሲማ  የወለጋ ሙዚየም ምስረታ ከነበራቸው ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው ፡፡

እሳቸው እንዳሉት ሙዚየሙ የተመሰረተው በቀድሞ ወለጋ ክፍለ ሀገር ሥር ከሚገኙ ስድስት አውራጃዎች የሕዝቡን ባህልና ታሪክ የሚያንጸባርቁ ቅርሶችን  በማሰባሰብ ነው፡፡

በወቅቱ ከየአውራጃው ለስብሰባ በሚመጡና በሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ሙዚየሙ ይጎበኝ  እንደነበር አስታውሰው፣ ለውጥ ከመጣ ወዲህ ግን የተጨመሩ ቅርሶች እንደሌሉ ጠቁመዋል፡፡

ወደፊትም በየወረዳዎች ተጨማሪ ቅርሶችን በማሰባሰብ ማጠናከርና ህዝቡም ባህሉን እንዲያውቅ  ማድረግ እንደሚገባ አመልክተው፣ የማስተዋወቁ ሥራ በመቀጠል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችና ኅብረተሰቡ ሲጎበኙ መመልከታቸው የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ገለታ ቴሶ የተባሉት የሙዚየሙ ሠራተኛ በበኩላቸው ''ሙዚየማችን ከዚህ በፊት እምብዛም አይታወቅም ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም መሥሪያ ቤት ሠራተኞች በማስተዋወቅ ተማሪዎችና ድርጅቶች መጥተው እየተመለከቱት ነው” ብለዋል።

ሙዚዩሙ በመንግሥት ወጪ እድሳት እንደተረገለት ሁሉ፤ የራሱ የሆነ  በጀት፣ ጥበቃና በቂ አስጎብኚ ተመድቦለት ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ሙዚየሙ የሕዝብና የአገርን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች የያዘ ትልቅ ሀብት በመሆኑ  አሁን ባሉት ሁለት አስጎብኚዎች ብቻ ቀኑን ሙሉ መሸፈን እንደሚከብድ ገልጸው፣ ''ኅብረተሰቡና መንግስትም ሊደጉሙት  ይገባል” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከምስራቅ ወለጋ  መስህቦች  መካከል  የወለጋ ሙዚየምና  የንጉስ ኩምሳ ሞረዳ ቤተ መንግስት  ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም