የአለም ከተማ-አቡስ የአስፓልት መንገድ ግንባታ አፈጻጸም 85 ነጥብ 8 በመቶ ደርሷል

88

አዲስ አበባ የካቲት 7/2011ግንባታው የዘገየው የአለም ከተማ-አቡስ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት አፈጻጸም 85 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

አለም ከተማ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በመርሐቤቴ ወረዳ ትገኛለች።

ባለስልጣኑ በየካቲት 2005 ዓ.ም የተጀመረውን የዚህን መንገድ ግንባታ ሂደትና አፈፃፀም ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን አስጎብኝቷል።

ግንባታውን በመከወን ላይ የሚገኘው ገምሹ አገር በቀል የሥራ ተቋራጭ ሲሆን የምህንድስና ቁጥጥርና የማማከር ሥራው ደግሞ በኮር ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ይከናወናል።

ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተሰራ ያለው ይህ የ48 ኪሎ ሜትር መንገድ የጎን ስፋቱ በአለም ከተማ 21 ሜትር በገጠር ደግሞ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 10 ሜትር ነው።

የመንገዱ ግንባታ ከተጀመረበት 2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥር 2011 ዓ.ም ድረስ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 40 ነጥብ 89 ኪሎ ሜትር ሲሆን በመቶኛ ሲሰላ 85 ነጥብ 8 መድረሱ ነው የተገለፀው።

ይሁን እንጂ መንገዱን ለማጠናቀቅ አስቀድሞ የ3 ዓመት ውል ታስሮ የነበረ ቢሆንም አካባቢው ተራራማ በመሆኑና የመሬት መንሸራተት በማስከተሉ የዲዛይን ለውጥ ተደርጓል፤ በዚህ ሳቢያም ባለስልጣኑ 603 ተጨማሪ ቀናት ለስራ ተቋራጩ ፈቅዷል።

ሆኖም የስራ ተቋራጩ በተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ ሥራውን ማጠናቀቅ ባለመቻሉ እስከ ሰኔ 2011 ዓ.ም አጠናቆ ማስረከብ እንዲችል ሌላ ተጨማሪ ጊዜ መሰጠቱን ባለስልጣኑ ገልጿል።

ኢዜአ መንገዱን በተሰጠው ጊዜ ማጠናቀቅ ያልተቻለው ለምንድነው? ሲል የገምሹ በየነ መንገድ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ባለቤት አቶ ገምሹ በየነን ጠይቆ

በሰጡት ምላሽ መንገዱ ከፍተኛ የሆነ የዲዛይን ችግር ያለበት በመሆኑ በርካታ የዲዛን ለውጦች በመደረጋቸው መጉዋተቱን ተናግረዋል፡፡

የበኮር ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ጂኦ ቴክኒካል ኢንጅነር አማካሪ መሀንዲስ አምደሚካኤል መንክር በበኩላቸው የመንገዱ ግንባታ  በተፈጥሯዊ መልክዓ ምድሩ ከ90 በመቶ በላይ ተራራማና ገደላማ በሆነ አካባቢ መሆኑ 'ለመዘግየቱ ምክንያት ነው' ብለዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ምርምር ማዕከል ተጠባባቂ ቡድን መሪ አቶ አህመድ ሂረዲን በበኩላቸው መንገዱ ከመሰራቱ በፊት ለምን ጥናት አልተደረገም ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በተፈጥሮ አደጋዎች እንጂ ጥናቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የመንገዱ ተገንብቶ መጠናቀቅ የመርሐቤቴ እና መንዝ ቀያ ወረዳን ከማስተሳሰር ባሻገር አካባቢው በጤፍ፣ ማሽላና ስንዴ አምራችነት የሚታወቅ በመሆኑ አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን በቀላሉ ወደ ገበያ እንዲያደርሱ ዕድል ይፈጥራል።

ቀደም ሲል በአካባቢው ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ባለመኖሩ ህክምና ለማግኘት ወደ አለም ከተማ የሚጓዙ የአካባቢው ነዋሪዎች መንገዱ ሲጠናቀቅ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም በአጭር ጊዜ ወደ ህክምና ቦታ እንዲደርሱም ያስችላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም