የፕሪሚየር ሊጉ ተስተካካይ ጨዋታዎች ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ

666

አዲስ አበባ የካቲት 7/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታዎች የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብር የካቲት 5 ቀን 2011 ዓ.ም መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች የተራዘሙ ጨዋታዎች በመኖራቸው ነው ተስተካካይ ጨዋታዎቹ የሚካሄዱት።

ቅዳሜ የካቲት 9 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ በ10 ሠዓት ላይ ይጫወታሉ።

መከላከያ በፕሪሚየር ሊጉ እስካሁን 13 ጨዋታዎችን አድርጎ በ16 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ተጋጣሚው ድሬዳዋ በተመሳሳይ 13 ጨዋታዎችን አድርጎ 14 ነጥብ በመሰብስብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የጨዋታው አሸናፊ በወራጅ ቀጠና ከሚገኙ ክለቦች በነጥብ እንዲርቅና ነጥቡን እንዲያሻሽል ይረዳዋል።

ቅዳሜ ጅማ አባ ጅፋር በጅማ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሠዓት ደደቢትን ያስተናግዳል።

የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋር እስካሁን በሊጉ ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች 14 ነጥብ ሰብስቦ 13ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ተጋጣሚው ደደቢት 14 ጨዋታዎችን አድርጎ 4 ነጥብ ብቻ በመሰብሰብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዟል።

ጅማ አባ ጅፋር የነገውን ጨምሮ አራት ተስተካካይ ጨዋታ ያለው ሲሆን ደደቢት የነገውን ጨምሮ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ አለው።

እሁድ የካቲት 10 ቀን 2011 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉ መሪ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሠዓት ከባህርዳር ከተማ ጋር ይገጥማል።

መቐለ ሰብዓ እንደርታ ባህርዳርን ካሸነፈ ከተከታዩ ሲዳማ ቡና ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ከፍ በማድረግ የሊጉን መሪነት ማጠናከር የሚችል ሲሆን በአንጻሩ ባህርዳር ከተማ ካሸነፈ አሁን ካለበት ስድስተኛ ደረጃ ወደ አራተኛ ከፍ ማለት ይችላል።

በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ከሚካሄዱት ሶስት ተስተተካይ ጨዋታዎች ውጪ ቀሪ አምስት ተስተካካይ ጨዋታዎች እስከ የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄዱ ይሆናል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ29 ነጥብ ሲመራ ሲዳማ ቡና በ27 ነጥብ ሁለተኛ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ26 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ደቡብ ፖሊስ፣ ስሑል ሽረና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።

የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ በ11 ጎል ሲመራ፣ የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤል በ10 ፣ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በዘጠኝ ግቦች ይከተላሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም