በኢሉአባቦር ዞን 200 ሄክታር መሬት በኖራ ታክሞ ወደ ልማት ገብቷል

66

መቱ ጥር 7/2011 በኢሉአባቦር ዞን  200 ሄክታር መሬት በኖራ ታክሞ  ለልማት መዋሉን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌታሁን ለገሰ እንዳሉት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በአሲድ ተበኖራ ከታከመ በኋላ ወደ ልማት የገባው በ11 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኝ የ748 አርሶ አደሮች ማሳ ነው ። 

መሬቱ በአሲዳማነት መብዛት ምርታማነቱ ቀንሶ እንደነበር አስታውሰው፣ በኖራ ከታከመ በኋላ በቆሎ፣ ማሽላና ጤፍ እንደለማበት ተናግረዋል፡፡

መሬቱን ለማከም  ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ ጥቅም ላይ እንደዋለም አቶ ጌታሁን አስታውሰዋል፡፡

አንድ ጊዜ በኖራ የታከመው መሬት እስከ አምስት ዓመታት ድረስ ምርታማነቱን ጠብቆ  እንደሚቆይ ተናግረዋል፡፡

በማሳ ላይ የአፈር ተሸርሽሮ ማለቅና አንድ ዓይነት ሰብል አከታትሎ መዝራት ለአሲዳማነት መፈጠር ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ  ምክትል ኃላፊው አመልክተዋል ፡፡

ሰብል አፈራርቆ በመዝራትና የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም ለምነቱን መመለስ እንደሚቻል ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

የተፈጥሮ ማዳበሪያን የሚያብላሉ የትል ዝርያዎች በአርሶ አደሮች የማሰልጠኛ ጣቢያዎች ተራብተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል።

ዝርያዎቹን በመጠቀም የሚዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ የአፈር ለምነትን የሚያሳድግ ከመሆኑም በተጨማሪ ጊዜና ጉልበት እንደሚቆጥብ አስረድተዋል፡፡

ለዚህም  በ31 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ በተዘጋጁ ማሳቆችና በአንድ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ጣቢያ ስልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ዓመትም ከወረዳዎች 503 ዓይነት የአፈር ናሙና ወደ በደሌ የአፈር ላቦራቶሪ ተልኮ ውጤቱ እየተጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል።

በሁሩሙ ወረዳ ጋባ ቀበሌ አርሶአደር ጉታ ፍሪሳ በሰጡት አስተያየት ለበርካታ ዓመታት ሰብል ያላበቀለ አንድ ጥማድ የሚሆን መሬታቸው በኖራ ከታከመ በኋላ ጤፍ እያለሙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአፈርን ለምነት ጠብቆ ለማቆየት ሰብል አፈራርቀው እንደሚዘሩና የተፈጥሮ ማዳበሪያ  እንደሚጠቀሙም ተናግረዋል፡፡

በኢሉአባቦር ዞን 13 ወረዳዎች በየዓመቱ 145 ሺህ ሄክታር መሬት በበልግና መኽር ወቅቶች በሰብል ይለማል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም