ሠራዊቱ ለጠላቶቹ የፍርሃት ምንጭ ለኢትዮጵያዊያንና ወዳጆቿ ኩራት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

100

አዲስ አበባ የካቲት 7/2011 የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለጠላቶቹ የፍርሃት ምንጭ፤ ለኢትዮጵያዊያንና ወዳጆቿ ኩራት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ለአገርና ለህዝብ ታላቅ መስዕዋትነት የከፈለ ትልቅ ተቋም መሆኑንም ተናግረዋል።

7ኛው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን "ሕገ መንግስታዊ ታማኝነታችንንና ሕዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን" በሚል መሪ ሃሳብ አዳማ ላይ ተከብሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም "ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን በዘመናት ሁሉ ያጋጠሙትን የውጪም ሆነ የውስጥ ሉዓላዊነት ፈተናዎች በከፍተኛ ወኔና ቁርጠኝነት የተወጣ የአገር መከታና አለኝታ የሆነ ተቋም ውስጥ በማገልገላችሁ ኩራት ሊሰማን ሊሰማችሁ ይገባል" ብለዋል።

መከላከያ ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ባለፈችባቸው ጊዜያት ሁሉ በታላቅ ቁርጠኝነት ያለፈ ትልቅ ተቋም መሆኑንም አውስተዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በአገር ውስጥም ሆነ ሠላም ለማስከበር በሄደባቸው አገራት ህዝባዊነቱን ያስመሰከረ ምስጉን ሠራዊት እንደሆነም ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በተቋሙ የነበሩ ውስጣዊና ብልሹ የአሰራር ችግሮችና ክፍተቶችን ለማረም እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር አብይ ገልጸዋል።

በተቋሙ እየተሰራ ያለው ሪፎርም የሲቪል ቁጥጥርን በተቋሙ ውስጥ በማረጋገጥ ለፕሮፌሽናል መከላከያ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት አገር ጠባቂ በመሆኑ በህዝብ ምርጫ ለተወሰነ ጊዜ ከሚመረጡ የህዝብ ወኪሎች ጋር መለዋወጥ የለበትም ሲሉም ተናግረዋል።

መከላከያ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ ሆኖ ህዝባዊነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

በመከላከያ ሠራዊት ላይ የሚካሄደው የስም ማጥፋትና የጅምላ ፍረጃ መቆም እንዳለበትና በዚህ ተግባር የተሰማሩ አካላትም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባም እንዲሁ።

የመከላከያን የቴክኖሎጂ አጠቀቀም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሳይበር እና በህዋ ምርምር መስክ ብቃትና ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች መሳተፍ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

'መከላከያን ለማዘመን ጊዜ ይጠይቃል፣ በአንድ ወቅት የሚሆን ጉዳይ አይደለም፣ ከዘመን ጋር አብር መዘመንና ሠራዊቱም በየወቅቱ ራሱን ማብቃት አለበት' ብለዋል።

በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ የተለያዩ አገልግሎቶች ሰጥተው ላለፉ አባላት ክብር መስጠት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

መከላከያ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ህዝቡም በየደረጃው ክብር ሊሰጠው እንደሚገባም አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም