የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች የአገር መከላከያ ሠራዊት ገድሎችን ለማስረጽ እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ

104

አዲስ አበባ የካቲት 7/2011 የጥበብ ሙያተኞች በኪነ-ጥበብ ስራዎቻቸው የአገር መከላከያ ሠራዊት ገድሎችን በህብረተሰቡ ዘንድ ለማስረጽ እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

ሰባተኛው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን "ሕገ መንግስታዊ ታማኝነታችንንና ሕዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን" በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ስታዲየም ተከብሯል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የቀድሞ የሠራዊቱ አመራሮችና የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለ ስልጣን /ኢጋድ/ አገራት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ታድመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የአሜሪካው አንጋፋ የፊልም ተቋም 'ሆሊውድ' የአሜሪካን ሠራዊት የጀግንነት ታሪኮች ለዜጎች በማስረጽ ረገድ በርካታ ስራዎችን መስራቱን አውስተዋል። 

ሆሊውድ አሜሪካዊያን በተሸነፉባቸው የጦር አውደ ውጊያዎች ሳይቀር የወታደሮቻቸውን ጀግንነት ማጉላት መቻሉን ገልጸው ይህም 'የአሜሪካ ወታደሮች ከአገራቸው ባለፈ በዓለማችንም ላይ የአገር ወዳድነት ምሳሌ እንዲሆኑ አስችሏል' ነው ያሉት።

"በእኛም አገር ያሉ የጥበብ ባለሙያዎች በኪነ-ጥበባዊ ስራዎቻቸው የሠራዊታችን ገድሎች ለህዝብ እንዲደርሱ ሊሰሩ ይገባል" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በቲያትርና በፊልሞች ላይ የሚቀረጹ የሠራዊት ገጸ ባህሪያት ለሚያስተላልፉት መልዕክት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሠራዊቱ አመራሮችም ከጥበብ ባለሙያዎች ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ነው መልዕክት ያስተላለፉት። 

ከደርግ ውድቀት በኋላ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የካቲት 7 ቀን 1988 ዓ.ም መመስረቱን ምክንያት በማድረግ ካለፉት ሰባት ዓመታት ጀምሮ ዕለቱ የመከላከያ ሠራዊት ቀን ሆኖ በየዓመቱ እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም