በሐረር ከተማ ጀጉላ ሆስፒታል የወደቀውን ሐውልት ወደ ቀድሞው ቦታ ለመመለስ እየተሰራ ነው

86

ሀረር የካቲት 7/2011በሐረር ከተማ ጀጉላ ሆስፒታል የወደቀውን ሐውልት ወደ ቀድሞው ቦታ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር አስታወቁ።

ዳይሬክተሩ አቶ ያሲር ዮኒስ  ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስረዱት በአደጋው ጉዳት የደረሰበትን የልዑል ራስ መኮንን መታሰቢያ ሐውልትን መልሶ ለመትከል ከሐረሪ ክልል መንግሥትና ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅቶ  እየተሰራ ነው።

ሆስፒታሉ ከሐረሪ ክልል  ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመቀናጀት  እየገነባው ያለው ሐውልት 10 ቶን ክብደት እንዳለው ገልጸዋል።

በሐውልቱ አደጋው የደረሰው  ሕሙማንን ለመውሰድ በመጣ አነስተኛ የጭነት መኪና ተገጭቶ በመውደቁ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

አደጋውን ያደረሰው አሽከርካሪና ተሽከርካሪም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አስታውቀዋል።

አደጋው በደረሰበት ወቅት በቦታው እንደነበሩ የሚናገሩት በሐረር ከተማ የአሚር ኑር ቀበሌ ነዋሪ አቶ መሐመድ አብዲ ሕሙማን ለመውሰድ የመጣ ተሽከርካሪ ሐውልቱ ተገጭቶ ሲወድቅ መመልከታቸውን ይናገራሉ።

''በሽተኛ ለመውሰድ የመጣ ተሽከርካሪ ወደኋላ በሚሄድበት ወቅት ረዳት ስለሌለው ሐውልቱን ገጭቶ ሊጥለው ችሏል። በቁጥጥር ሥርም ልናውለው ችለናል'' ያሉት የሆስፒታሉ ጥበቃ ሠራተኛ አቶ ተስፋሁን ዓለሙ ናቸው።

በአሁኑ ወቅትም ሐውልቱን  ወደ ቦታው ለመመለስ ሥራው እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሐውልቱን መልሶ ለማቆም በባለሙያዎች ርብርብ ሲደረግ ተመልክቷል።

በቀድሞው የምሥራቅ አርበኞች ሆስፒታል መልሶ ለማቆም የሚገነባው ሐውልት 117 ዓመታት ያስቆጠረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም