ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊት የሌለው አገር እንደ ድሃ አጥር ሌባውም ውሻውም የሚገባበት ነው ---አቶ ለማ መገርሳ

109

አዳማ የካቲት 6/2011”ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊት የሌላት አገር እንደ ድሃ አጥር ሌባውም ውሻውም የሚገባበት በመሆኑ ሁላችንም የመከላከያ ሰራዊታችን ለማጠናከር መስራት አለብን” ሲሉ የኦሮሚያ ክልላዊ ፕሬዘዳንት ለማ መገርሳ ገለፁ ።

ርዕሰ-መስተዳደሩ ይሔንን ያሉት ሰባተኛው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን በማስመልከት "ህገ መንግስታዊ ታማኝነታችንና ህዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን" በሚል መሪ ሀሳብ በአዳማ ከተማ በተካሔደ የፓናል ውይይት ላይ ነው።

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ትላንት በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያዊ ሠራዊት መሆኑን በተግባር ጭምር እያረጋገጠ መጥቷል።

ጠንካራ የሀገር የመከላከያ ሠራዊት ባይኖር ኖሮ አሁን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተነሱ ካሉ ችግሮች አንጻር ኢትዮጵያ የመፈራረስ ዕጣ ፈንታ ያጋጥማት እንደነበረም ገልጸዋል።

ኢትዮዽያ የምትገኝበት ቀጠና የደህንነት ስጋት የሚታይበት መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ  በአገር ውስጥም ቢሆን በየቦታው የሚስተዋሉ የአክራሪነትና ሽብርተኝነት ተግባራት እንዲሁም የወሰን ግጭቶች ስጋት መፍጠራቸውን አስረድተዋል።

ስጋቱ  ወደ ከፋ ችግር እንዳይሸጋገር የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ኢትዮዽያና ህዝቦቿን እየታደገ እንደሚገኝ አቶ ለማ ተናገረዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተላበሰው ጠንካራ ስብዕና ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያንም ጭምር አለኝታ እየሆነ መጥቷል።

የሀገሪቱን መልካም ገጽታ በመገንባትና በዓለም አቀፍ ደረጃ  ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነቷ ከፍ እንዲል ከማድረግ አንጻር የጎላ ሚና መጫወቱንም ነው የጠቆሙት።

”ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት የሌለው አገር እንደ ድሃ አጥር ይቆጠራል፤ ምክንያቱ ደግሞ ሌባውም ውሻውም ስለሚገባበት ክብር የለውም" ያሉት አቶ ለማ፣ የጋራና ጠንካራ የብረት አጥር የሚሆን የመከላከያ ሠራዊት ለመገንባት ሁሉም አካል ለሠራዊቱ ሞራልና ተገቢውን ክብር በመስጠት ሊደግፈው እንደሚገባ ገልጸዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሰዓረ መኮንን " መከላከያ ሠራዊት በለውጥ ሂደት " የበሚል የውይይት መነሻ ጹሁፍ አቅርበዋል ።

የመከላከያ ሠራዊቱ በጀመረው የለውጥ ሂደት ህገመንግስታዊ ተልዕኮውን በብቃት የሚወጣ፣ ሙያዊ ብቃት ያለውና በሰላም ማስከበሩ ሂደት ጠንካራ የተልዕኮ አፈጻፀም አቅም የገነባ ሠራዊት ለመገንባት እንደሚሰራም አመልክተዋል።

በተጨማሪም በለውጥ ሂደቱ እስከ ጦር ኮሌጅ መክፈት የሚደርስ የአቅም ግንባታን ያካተተ፣ አገሩንና ህዝቡን በምጣኔ ሀብትና በቴክኖሎጂ የሚደግፍ ዘመናዊና በሙያው የበቃ ሠራዊት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

" የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪካዊ ጉዞ ከትናንት እስከ ዛሬ " የሚል የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት ደግሞ የአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ይልማ መርዳሳ ናቸው ።

የአገሪቱን የአየር ኃይል ክልል በማንኛውንም ሁኔታና ጊዜ የመከላከልና የመጠበቅ አቅም ያለው የለውጥ ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ብርጋዴር ጀኔራሉ ባቀረቡት ጽሑፍ አመለክተዋል።

ለሠራዊቱ ቅርብ የአየር ድጋፍ በመስጠት ለውጊያ የተመረጡ ኢላማዎችን መደምሰስ፣ አስተማማኝ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዲሁም በተፈጥሮና በሰው ሰው ሰራሽ አደጋ ወቅት ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በካባቢያዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሰላም ማስከበር ግዳጅ በብቃት መወጣት፣ የሳይበር ተጋላጭነት መከላከልና የማጥቃት አቅም ማጠናከር ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ብርጋዴር ጄነራል ይልማ አስረድተዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ ሚኒስትሮች፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባት አርበኞች፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችና ከ2 ሺህ በላይ የአዳማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ከጥር 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሲከበር የቆየው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲዮም በአገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት በማክበር እንደሚጠናቀቅ በመከላከያ ሚኒስቴር የኢንዶክትሬሽን ዳይረክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም