ዐቃቤ ህግ በአቶ ቴዎድሮስ አዲሱ ላይ የ15 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ ጠየቀ

61

አዲስ አበባ የካቲት 6/2011 በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩት አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) ላይ ዐቃቤ ህግ የ15 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ ጠየቀ።

መርማሪ ፖሊስ በአቶ ቴዎድሮስ ላይ ሲያደርግ የነበረውን ምርምራ አጠናቆ የምርመራ መዝገቡን ዛሬ ለዐቃቤ ህግ አስረክቧል።

ዐቃቤ ህግ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት እንደገለጸው፤ ተጠርጣሪው አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ ባላቸው የህትመት ድርጅት ከኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅና ከሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ጋር የመማሪያ መጻህፍትን ለማተም ውል ፈጽመው እንደነበረ ገልጿል።

ሆኖም ተጠርጣሪው ከኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅና ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጋር በመመሳጠር በውሉ መሰረት መጽሐፉን ሳያስረክቡ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ቅድሚያ ክፍያ እንደተከፈላቸው ዐቃቤ ህግ ለችሎቱ አስረድቷል።

በዚህ መሠረት አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ በመንግስትና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ዐቃቤ ህግ አስረድቷል። 

የተፈጸመው ወንጀል ውስብስብና ከባድ ከመሆኑም በላይ የተፈጸመው ወንጀል ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ስለሆነ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎችን አሳባስቦ በማጠናቀቅ በቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) ክስ ለመመስረት  የ15 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ግለሰቡ የተጠረጠሩብት ወንጀል ከባድ የሙስና ወንጀል ሲሆን የዋስትና መብት የሚያስከለክል በመሆኑ የተጠርጣሪው የዋስትና መብት ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲደረግለት ዐቃቤ ህግ ችሎቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪው አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ የህትመት ድርጅታቸው ለሰባት ወራት መታገዱንና ድርጅቱ መዘረፉን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።

የፍርድ ቤት እገዳ ሳይኖር ድርጅታቸው መታገድ እንደሌለበት ያመለከቱት አቶ ቴዎድሮስ የሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ የህትመት ስራ አሰርቷቸው 7 ሚሊዮን ብር እንዳልተከፈላቸውም ተናግረዋል።

በሶማሌ ክልል ፍርድ ቤት የታገደው የአቶ ቴዎድሮስ የህትመት ድርጅት ፖሊስ ለተጠርጣሪው ማሳወቅ እንደነበረበት የገለጸው ችሎቱ ከዚህ በኋላም ተጠርጣሪው ማወቅ የሚገባቸውን መረጃዎች ፖሊስ በወቅቱ እንዲያሳውቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ በተጠየቀው የ15 ቀናት የክስ መመስረቻ ጊዜ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ከሰዓት በኋላ ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ በሌላ መዝገብ  ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በጅግጅጋ እና አካባቢው ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ ቢሆንም ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምርመራውን ባለማጠናቀቁ የተጠርጣሪው ጠበቃ የግለሰቡን ፍትህ የማግኘት መብት የሚጎዳ መሆኑን ፍርድ ቤቱ አመዛዝኖ የክስ መዝገቡ እንዲዘጋ መጠየቁ ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱም ከተጠርጣሪው ጠበቃ የቀረበውን የክስ መዝገቡ እንዲዘጋ ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ተጠርጣሪው በ80 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ውሳኔ መስጠቱ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ አቶ ቴዎድሮስ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሄደባቸው በመሆኑ ከእስር አልተፈቱም።

በሌላ በኩል በሙስና ወንጀል የተጠርጠሩት የቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር የነበሩት የሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘው ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

ፖሊስ በአቶ ኢሳያስ ዳኘው ላይ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪው አቶ ኢሳያስ ዳኘው በኢትዮ ቴሌኮም የኤን ጂ ፒ ኦ ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ከኢትዮ ቴሌኮም ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ኢ ዲ ኤም ለተባለ የውጭ አገር ድርጅት ያለ ምንም ጨረታና ውድድር የውል ስምምነት እንዳደረጉና ለፕሮጀክቱ 12 ሰራተኞችና አማካሪዎች ከ2001 እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ በነበረው ጊዜ በሰዓት ከ125 እስከ 150 ዶላር ለእያንዳንዳቸው እንዲከፈል ማድረጋቸውን ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

እንዲሁም የኢ ዲ ኤም ድርጅት ስራ አስኪያጅም ተገቢ ያልሆነ ክፍያ ሲፈጸምላቸው እንደነበረም ፖሊስ ገልጿል።

አቶ ኢሳያስ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ድርጅቱ ርክክብ ሳይፈጽም የ10 በመቶ ክፍያ እንዲፈጸም አድርገዋልም ብሏል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ክፍያዎች የሚፈጸሙት በቦርድ አባላት ትዕዛዝ እንጂ በግለሰብ ትዕዛዝ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ከሌሎች መስሪያ ቤቶች በተሻለ መልኩ የፕሮጀክት ኮንትራት አስተዳደር እንዳለውና የተቋሙ ፕሮጀክቶች ለእንዲህ አይነት የወንጀል ድርጊት የተጋለጡ አይደሉም ብለዋል።

ተጠርጣሪው ከዚህ በፊት በተጠረጠሩበት ወንጀል በዋስ እንዲወጡ ፍርድ ቤቱ ወስኖ ከእስር ቤት ሊወጡ ሲሉ ተጨባጭ ማስረጃ በሌለበት አዲስ የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል መባሉ እስር ቤት እንዲቆዩ ለማድረግ እንደሆነም ለችሎቱ አስረድተዋል።

ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ችሎቱን መጠየቁ አግባብ እንዳልሆነና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግም ተከራክረዋል።

ተጨባጭ መረጃ በሌለበት በተጠርጣሪው ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁ ደንበኛው እንዲጉላሉ በማድረግ የተፋጠነ ፍትህ እንዳያገኙ ፖሊስ እያደረገ በመሆኑ ተጠርጣሪው አፋጣኝ ፍትህ እንዲያገኙ ጠበቆቹ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ በጠየቀው ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ነገ ለሰዓት በኋላ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

አቶ ኢሳያስ ዳኘው ከዚህ በፊት ለሜቴክ የተሰጠን ውል በማሻሻልና ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ በመንግስትና በህዝብ ሃብት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው በተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል ፍርድ ቤቱ በ200 ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቁና ከአገር እንዳይወጡ ለኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መምሪያ እገዳ እንዲተላለፍ መወሰኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም