ዩኒቨርሲቲዎች በችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ተገለጸ

202

ሚዛን የካቲት 6/2011 ዩኒቨርሲቲዎች የማህበረሰቡን ችግር በሚፈቱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው ተጠቆመ።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው ስምንተኛው ሀገር ዓቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በመካሄድ ላይ ነው።

በኮንፈረንሱ ላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ችግር ፈቺ በሆኑና ተጨባጭ ለውጥ በሚያስገኙ የምርምር ተግባራት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የጥናት፣ ምርምርና ማህበረሰብ ድጋፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ምትኩ ወልደሰማያት እንዳሉት በኮንፈረንሱ ላይ 39 ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

ጽሁፎቹ በአካባቢ ሀብት ጥበቃ፣ ብዝሃ ባህል፣ በጤናና ሌሎችም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ በመድረኩ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

"በኮንፈረንሱ ላይ በተመራማሪዎች የሚቀርቡ የምርምር ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ ወደተግባር የመቀየር ሥራ ይሰራልም" ብለዋል። 

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሙሉ ጌታ በበኩላቸው የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ጉባኤ ከማዘጋጀት ባሻገር ምርምርን ወደ ተግባር መለወጥ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

"በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች ብዙ ወጪ የተደረገባቸው በመሆኑ ጥቅም ላይ ሳይውሉ ለብክነት መዳረግ የለባቸውም" ብለዋል።

ተመራማሪዎችም በዋናነት ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ሀገርንና ማህበረሰቡን ከችግር ሊታደጉ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ አተኩረው መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው ስምንተኛው ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ኮንፈረስ ነገም የሚቀጥል ሲሆን " ጥናትና ምርምር ለሀብት አጠቃቀምና ለማህበራዊና ምጣኔ ሀብት ዕድገት " የሚል መሪ ሃሳብ እንዳለው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም