123ኛው የዓድዋ ድል በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተጠቆመ

51

አክሱም የካቲት  6/2011 ኢትዮጵያ ወራሪው የጣሊያን ጦር ድል ያደረገችበትን 123ኛ ዓመት የዓድዋ ድል በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተገለጸ።

የአድዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ዘስላሴ ዘርአብሩክ ለኢትዽያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አባቶች ወራሪውን የጣሊያን ጦር ድል ያደረጉበት የአድዋ ድል በዓል በደመቀ ስነ ስርዓት ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል።

በዓሉ የአባቶች ጀግንነትንና ለአገር አንድነት የነበራቸውን ፍቅር ወጣቶች በሚማሩበት መንገድ እንደሚከበር አስታውቀዋል።

ቀደምት አባቶች ኋላ ቀር መሳሪያ ታጥቀው ወራሪውን የጣሊያን ጦር የተዋጉባቸው ቦታዎችን መጎብኘት የምርሃ ግብሩ አካል መሆኑንም አመለክተዋል።

የጦርነት ስፍራዎቹን የአሁኑ ትውልድ በአግባቡ እንዲያቃቸውና ለቱሪስት መስህብ አገልግሎት እንዲውሉ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚካሄድም ገልጸዋል፡፡

በበዓሉ ከ500 በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት ችቦ የማብራትና ባህላዊ ትጥቅን በመታጠቅ የጦርነት አውድማ የነበረው የሶሎዳ ተራራን የመውጣት ስነ ስርዓት እንደሚካሄድም ተናግረዋል።

የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር የበዓሉ አካል መሆኑን ከንቲባው አስታወቀዋል።

"የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር አፍሪካውያን ተምሳሌት በመሆኑ አዲሱን ትልድ የሚያስተምር ዘጋቢ ፊልም ለዕይታ ይቀርባል ብለዋል።

በዓሉን በድምቀት ለማክበር ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ  የተለያዩ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን የገለጹት ከንቲባው የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን የሚገኙበት  የፓናል ውይይት እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።

የአድዋ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ዮርዳኖስ ሙሉ በበኩላቸው በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶች ለመቀበል ቤታቸውን በማሳደስ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የምግብ ዋጋና ሌሎች አገልግሎቶች ላይ ጭማሪ እንዳይደረግ ክትትል ለማድረግ ከህብረተሰቡ መመረጣቸውን የገለጹት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ማርታ ዘመንፈስ ቅዱስ ናቸው።

122ኛው የአድዋ ድል በዓል “አድዋ በአብሮነት የአሸናፊነት ተምሳሌት!” በሚል መሪ ቃል የካቲት 22 እና 23 ቀን 2010 ዓ.ም በትግራይ ክልል አደዋ ከተማ መከበሩ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም