በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው የሰላም ፎረም ለመማር ማስተማሩ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተገለጸ

102

ክልል የካቲት 6/2011 በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው የማህበረሰብ አቀፍ የሰላም ፎረም የመማር ማስተማሩን ሥራ በሁሉም የተቋሙ ካምፓሶች በተያዘለት መርሀግብር ለማስቀጠል አስተዋጽኦ ማድረጉን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ገለጹ። 

መምህራንና ተማሪዎች በበኩላቸው ችግሮችን ተቀራርበው በመፍታት ለመማር ማስተማሩ ሥራ ውጤታማነት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ አመንቴ ለኢዜአ እንዳሉት በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መሀል የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ዘንድሮ የተቀናጀ  ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

በዚህም ውጤታማ ሆነዋል ባሏቸው የወሊሶ ፣ ጉደርና  አዋሮ ካምፓሶች የዘመኑ ትምህርት በጥሩ ሁኔታ እንደቀጠለ ተናግረዋል፡፡

ሰላም ከሌላ ትምህርት እንደሚቆምና ይህም ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸውን ከመጉዳት ባለፈ በሀገርም ላይ ጫና ስለሚፈጥር ሁሉም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መረባረብ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖርም ተማሪዎችና መምህራን የሚመሩት እንዲሁም የመስተዳደር አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የአምቦ አካባቢ ማህበረሰብን ያቀፉ የሰላም ፎረሞች እንዲቋቋሙ መደረጉን  አመልክተዋል፡፡

ከፎረሞቹ ጋር በቅንጅት መስራቱ ሰላማዊ የመማር ሥራ በተያዘለት መርሀግብር  መሰረት ለማስቀጠል የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ታደሰ እንዳሉት ከሁሉም በላይ ተማሪዎች  በምክንያታዊነት መንቀሳቀስና መምህራንም አባታዊ  ምክር በመስጠት የድርሻቸውን ከተወጡ ሰላምን አጠናክሮ ማስቀጠል ይቻላል፡፡

"ተማሪዎች የአንድነትና የፍቅር ድልድይ በመሆን ተቀናጅተው መንቀሳቀስ ከቻሉ የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ዓላማ ማሳከት ይቻላል" ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የኢዲኩይሽናል ፕላንግ ትምህርት ክፍል መምህርት መስታወት በየነ በበኩላቸው ከእዚህ ቀደም በተቋሙ ውስጥ አንዳንድ ውዥንብሮች ይሰራጩ እንደነበር አስታውሰዋል።

በመምህራን፣ ተማሪዎችና  የአካባቢው ማህበረሰብ የጋራ ጥረት ችግሮችን በመፍታት በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ  የመማር ማስተማር ሥራ ማስቀጠል እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

እንደሀገር ለውጥ እንዲመጣ  የአምቦ ዩኒቨርሲቲና  የአካባቢው ማህበረስብ  ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በተቋሙ የትምህርት ጥራት ማስጠበቂየና ማበልጸጊያ ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ከበደ ሶርሳ ናቸው፡፡

የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህሩ ዳዊት ነገሪ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ተከስቶ የነበረው መጠነኛ ችግር በመፈታቱ አሁን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

“ እኔ እንደመምህር ተማሪዎች ሲጋጩ በማረጋጋትና በመምከር የድርሻዬን ስወጣ ነበር፤ ከዚህ በፊት መምህራን ግጭት ሲፈጠር ይደበቁ ነበር።  አሁን ግን ጣልቃ በመግባትና በመፍታት እንደሀገር የመጣውን ለውጥ በማጠናከር አስተዋጽኦ አድርገውል” ብለዋል፡፡

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ኡሊ በዳኔ በበኩሏ የተማሪዎችን ችግር ከተቋሙ አስተዳደር ጋር ተቀራርበው መፍታት በመቻላቸው በአሁኑ ወቅት የትምህርት መረሃ ግብሩ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግራለች።

ቀደም ሲል የነበረው የተወሰነ አለመረጋጋት በመስተካከሉ ትምህርታቸውን በተገቢው ሁኔታ እየተከታተሉ መሆናቸውን የገለጸችው የሦስተኛ ዓመት የህክምና ተማሪ ሀዊ ንጉሴ ናት።

በዩኒቨርሲቲው የማርኬቲንግ ማኔጅመንት የሦስተኛ ዓመት ተማሪ አወል ከድር በበኩሉ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከፖለቲካ ጋር ሳይገናኙ ጊዜያቸውን ለመጡለት የትምህርት ዓላማ ብቻ ማዋል እንዳለባቸው አመልክቷል፡፡

የኮሚኒቲ ዴቬሎፕመንት ተማሪ ፀሐይ ጌታሰው በጥቂት ተማሪዎች ቀስቃሽነት ተረብሾ የነበረው ግቢያቸው በአሁኑ ወቅት በመጣው ለውጥ ትምህርታቸውን ተረጋግተረው እየተማሩ መሆናቸውን ተናግራለች፡፡

" ተማሪዎች መብት እንዳለን ሁሉ ግዴታቸንንም ልናውቅ ይገባል" ብላለች፡፡

የግቢው  ፖሊስ  አባል ሰብለ ብርሁኑ በበኩሏ "  ቀደም ሲል የተወሰነ የተማሪዎች ሁካታ አስነስተው ነበር ፤ አሁን ሰላም ነው ፤ ከተማሪው ጋር እናትና ልጅ ግንኙነት ነው ያለን፤ ችግር ሲፈጠር አቅርበናቸው በመምከር ለመፍታት ባደረግነው ጥረት ውጤታማ ሆነናል ፤ ወደፊትም ይህንኑ እናስቀጥላለን" ብላለች፡፡

ከአምቦ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው "እኔ የማህበረሰቡ አባል በመሆኔ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ሆኜ ሌት ተቀን ስንሰራ ነበር፤ በዚህም ሰላም እንዲመለስ አድረገናል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

"የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩ አካላት ነበሩ" ያሉት አቶ ተስፋዬ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ኮሚቴ ተዋቅሮ ውይይት በመደረጉ በተማሪዎች መካከል እርስ በርስ የመቀራረብና የመተሳሰብ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ እና በተከታታይ የትምህርት መርሀግብር በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ በሦስተኛው ዲግሪ ከ25 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም