በአዲስ አበባ በሪል ስቴት ልማት ከተሰማሩት ድርጅቶች መካከል ግብር እየከፈሉ ያሉት 6 ብቻ ናቸው

150

አዲስ አበባ የካቲት 6/2011 በአዲስ አበባ ከተማ በመኖሪያ ቤት ግንባታ (ሪል ስቴት) ልማት ዘርፍ ከተሰማሩ 138 ድርጅቶች መካከል የሚጠበቅባቸውን ግብር እየከፈሉ ያሉት ስድስት ብቻ መሆናቸውን የአስተዳደሩ ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ።  

ከተማዋ ከመሬት፣ ከቤትና ከሌሎች ንብረቶች የምታገኘው የገቢ ግብር ከአጠቃላይ ገቢዋ አንድ በመቶ እንደማይሞላም ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደገለፁት የሪል ስቴት ግብር ከንብረት ግብር የሚመደብ ሆኖ ብዙ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ቢሆንም ከተማዋ ከዘርፉ የምታገኘው ግብር ግን በእጂጉ ያነሰ ነው።

https://youtu.be/UYU10xRfHmU
የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ

በከተማዋ በግል ባለሀብቶች እየተከናወነ ካለው ሰፊ የመኖሪያ ቤት ግንባታ አኳያ ከንብረት ግብር መሰብሰብ ከሚገባው ገቢ በታች ሆኖ ለረጅም ዓመታት ቆይቷልም ብለዋል።

ለገቢ ግብሩ ማነስ ምክንያት የሆነው ከ40 ዓመታት በላይ ሳይሻሻል የቆየው የገቢ ግብር አዋጁ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ ከተማዋ ከሪል ስቴት ግንባታ፣ ከመሬት፣ ከቤትና ሌሎች ንብረቶች የምታገኘው የገቢ ግብር ከአጠቃላይ ገቢዋ አንድ በመቶ አይሟላም።

በሌሎች አገሮች ያለው ልምድ የሚያሳየው የከተሞች ትልቁ ገቢ የንብረት ገቢ ግብር ቢሆንም የአዲስ አበባ ግን ከዚህ በተቃራኒው መሆኑንም ገልፀዋል።

የንብረት ገቢ ግብር የተጣለባቸው ዘርፎች አነስተኛ ከመሆናቸውም ባሻገር የሚጠበቅባቸውን ግብር እንደማይከፍሉ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በከተማዋ ግብር የማይነካቸውና ግብር ሊጣልባቸው የሚገባቸው ዘርፎች እንዳሉም ተናግረዋል። 

በተለይ በከተማዋ በስፋት በግል ባለሀብቶች ከሚከናወነው የመኖሪያ ቤት ግንባታ (ሪል ስቴት) አስተዳደሩ በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ የሚፈለገውን ገቢ ሳያገኝ መቅረቱን ተናግረዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ አስተዳደሩ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት መሰረት በመዲናዋ በሪል ስቴት ልማት ተሰማርተው ከሚገኙ 138 ድርጅቶች መካከል እስካሁን የሚጠበቅባቸውን ግብር የሚከፍሉት ስድስቱ ብቻ ናቸው።

ከደርጅቶቹ መካከል 27 የሚሆኑት አልፎ አልፎ ሲከፍሉ 105ቱ ግን እስካሁን የሚጠበቅባቸውን ግብር እየከፈሉ አይደለም።

የከተማ አስተዳደሩ በተያዘው በጀት ዓመት ከስድስቱ የሪል ስቴት አልሚዎች 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ብቻ ገቢ ማግኘቱን የገለጹት አቶ ሺሰማ ግብር ሳይከፍሉ የቆዩ አልሚዎች እስከ የካቲት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ከፍለው እንዲያጠናቅቁም አሳስበዋል።

ግንባታቸውን አጠናቀው ለነዋሪዎች ያስተላለፉ አልሚዎችም ለአስተዳደሩ ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል።

የሪል ስቴት አልሚዎቹ ከያዙት 4 ሚሊዮን 4 መቶ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ አኳያ ከሊዝ፣ ከመኖሪያ ቤትና ከቤት ማስተላለፍ የተገኘው የገቢ ግብር ግን ዝቅተኛ  ነው ብለዋል አቶ ሺሰማ።

አዲስ አበባ ከዘረፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ አስተዳደሩ ጥናት በማካሄድ አምስት ሰነዶችን በማዘጋጀቱ በቅርቡ ውይይት ተደርጎበት ከውይይቱ የሚገኘውን ግብዓት መሠረት በማድረግ የገቢ ግብር አዋጁን የማሻሻል ስራ ይሰራልም ብለዋል።

የመኖሪያ ቤት ግንባታ (ሪል ስቴት) አልሚዎች ከተፈቀደላቸው ይዞታ በላይ አስፋፍተው የያዙ፣ የሊዝ ግብር ያልከፈሉ፣ ግንባታ ጀምረው ያቆሙ፣ ከተፈቀደላቸው አገልግሎት ውጪ መሬቱን ለሌላ ዓላማ የሚጠቀሙና መሬቱን ለሦስተኛ ወገን ያስተላለፉ አልሚዎች መኖራቸው ተደርሶበታል።

በከተማዋ በሪል ስቴት ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን የግንባታ ሁኔታና ህጋዊነት የሚያጠና ግብረ ኃይል አዋቅሮ የዳሰሳ ጥናት ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል።

ከአስተዳደሩ መሬት ወስደው ግንባታ ያልጀመሩና መሠረት ብቻ አውጥተው ወደ ግንባታ ያልገቡ አልሚዎች ይዞታቸው እንዲነጠቅ መወሰኑንም የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም