በመቀሌ ተግባር ተኮር ትምህርት ያለ አግባብ እንደተቋረጠባቸው ተጠቃሚዎች ተናገሩ

46

መቀሌ የካቲት 6/2011 በመቀሌ ከተማ ተግባር ተኮር ትምህርት ያለ አግባብ እንደተቋረጠባቸው አንዳንድ ተጠቃሚዎች ገለጹ።

የሚመለከታቸው አካላት ትምህርቱ የተቋረጠው በባለድርሻ አካላት ቅንጅት ማጣት ነው ብለዋል።

ከተጠቃሚዎቹ  አንዳንዶቹ ለኢ ዜ አ  እንደተናገሩት በሕይወታቸው ላይ ለውጥ የሚያመጣው ትምህርት እስካሁን አልተጀመረም።ባለፉት ዓመታት የትምህርቱ መጀመሪያ ጊዜ  ከኅዳር አልፎ አያውቅም ነበር ብለዋል።

የትምህርቱ ተጠቃሚ ከሆኑት የከተማው ነዋሪዎች መካከል የሐውልት ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ብርሃን ንጉሰ አንዷ ናቸው።

ባለፈው የትምህርት ዘመን የጀመሩትን ትምህርት ዘንድሮ እንደተቋረጠባቸው ይገልጻሉ። በዚህም የጨበጡትን የመጻፍና የማንበብ ክህሎት እየረሱት መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በግልና በአካባቢ ጤና አጠባበቅ፣በግብርናና ምጣኔ ሀብት ይሰጥ የነበረውን ችግር ፈቺ የተግባር ትምህርት በኑሮአቸው ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ሲጠቀሙበት እንደነበር የገለጹት ደግሞ በመቀሌ የዓዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አባዲት ተወልደ ናቸው።

ትምህርቱ ካለው ጠቀሜታ ታይቶ እንዲቀጥል የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በመቀሌ ዞን መስተዳድር ምክር ቤት የሴቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ መድህን ሕሉፍ በከተማው ላለፉት ሁለት ዓመታት የተሰጠው ትምህርት በተለይ በሴቶች ሕይወት ተጨባጭ ለውጥ አምጥቶ ነበር።

በጤና አጠባበቅ ዘዴ፣በእርሻና  በንግድ መስኮች የተሰጠው ትምህርት በተግባር የተደገፈ ዕውቀታቸውን ለማሳደግና የመፃፍና ማንበብ ክህሎታቸውን እንዳዳበረው ይናገራሉ።

ትምህርቱ ሴቶች ድህነትን ለመታገል ለሚያደርጉት ቀጣይ ትግል ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ሊቀጥል እንደሚገባው አመልክተዋል።

እንዲሁም እናቶች መልካም ልምድ  የሚለዋወጡበትና የሚተዋወቁበት አጋጣሚ በማመቻቸትም ዋጋ እንዳለው ገልጸዋል።

ባለለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ምህረቱን እንዲያስቀጥሉ ሰብሳቢዋ አሳስበዋል።

በመቀሌ የሓውልት ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ አቶ ግርማይ አለም በበኩላቸው በባለድርሻ አካላት ቅንጅት ማነስ ምክንያት ትምህርቱ  መቋረጡን ተናግረዋል።

ባለድርሻ አካላቱ ያለባቸውን ችግር መገምገሙንና በዚህ ወርም  ትምህርቱ ለማስጀመር ዝግጅቱ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ትምህርቱ በአመራሮች ግድየለሽነት ምክንያት መቋረጡን የሚያወሱት ደግሞ በመቀሌ ከተማ የሰሜን ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ ወይዘሮ እየሱስ ገብረእግዚአሔር ናቸው።

በመሆኑም በአመራሮቹ የታየው ችግር እንዳይደገም መገምገሙንና ትምህርቱን ለማስጀመር የመምህራን ቅጥርና የተማሪዎች ምዝገባ በማካሄድ ላይ እንገኛለን ብለዋል አስተዳዳሪዋ።

በመቀሌ ዞን ትምህርት ፅህፈት ቤት የስርዓተ ትምህርት ኃላፊ አቶ ተስፋዮሃንስ ግደይ እንዳሉትም ነዋሪዎቹ ያቀረቡት ቅሬታ ለመፍታትና በባለድርሻ አካላት ቅንጅት ማጣት የተቋረጠው ትምህርት ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም