በባሌ ዞን ከ 255 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማልማት እየተሰራ ነው

65

ጎባ የካቲት 6 /2011 በባሌ ዞን በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ 255 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ልማት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሙዘየን ሱልጣን እንዳሉት የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራ እየተከናወነ ያለው በተመረጡ 250 ተፋሰሶች ላይ ነው።

ካለፈው ጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ በዞኑ 18 የገጠር ወረዳዎች እየተከናወነ ባለው የልማት እንቅስቃሴም ከ 400 ሺህ የሚበልጡ አርሶና አርብቶ አደሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

አቶ ሙዘይን እንዳሉት ለአንድ ወር በሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ ከ 52 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ እርከንና ጎርፍ መቀልበሻ ቦይ ለመስራት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።

ከእዚህ በተጨማሪ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት የተጎሳቆለ ከ 30 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ በመከለል መልሶ እንዲያገግም የሚደረግ መሆኑን ነው የተናገሩት።

እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም ከ100 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ በዞኑ ባለፉት ዓማታት በአርሶና በአርብቶ አደሩ ተሳትፎ በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የዞኑ የደን ሽፋን ጨምሯል።

ደርቀው የነበሩ በርካታ ምንጮችም መልሰው ከመፍለቃቸው በተጨማሪ ለግብርና ልማት ሥራ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱን ነው የጠቆሙት።

በዞኑ የዳዌ ቃቸን ወረዳ ከፊል አርብቶ አደር አህመድ ሱልጣን በበኩላቸው በጋራ ያከናወኑት የአፈርና ውሃ እቀባ ልማት ሥራ ለእንሰሶቻቸው የግጦሽ ሳርና መኖ በቅርበት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።

ባለፈው ዓመት ብቻ በአራት ዙር ያደለቧቸውን 20 ሰንጋዎች ለገበያ በማቅረብና 400 ሺህ ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢያችን በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ለመጥፋት ተቃርበው የነበሩ ምንጮች መልሰው ማገገማቸውንና በዚህም የመጠጥ ውሃ ችግራቸው መቀረፉን የገለጹት ደግሞ ሌላዋ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ ሀምዲያ አህመድ ናቸው።   

ቀደም ሲል በአካባቢያቸው የተፈጥሮ ሀብት በመጎዳቱ ምክንያት ከማሳቸው የሚያገኙት የግብርና ምርት ከመቀነሱ ባለፈ በተደጋጋሚ በጎርፍ ሲጠቁ መቆየታቸውን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር እሱማን በከር ናቸው፡፡

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የጎርፍ ተጋላጭነታቸውን ከመቀነስ ባለፈ በተከላሉ አካባቢዎች በሚለማው የእንስሳት መኖ እንሰሶቻቸውን በተሻለ መመገብ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

በባሌ ዞን ባለፉት አምስት ዓመታት ከ 356 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተቀናጃ የአፈርና ውሃ እቀባ መልማቱ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤትን ዋቢ በማድረግ የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም