በዩኒየን የገባነው የብድር መድን ዋስትና የእዳ ጫናችንን አስቀርቶልናል--- የኦፍላ ወረዳ አርሶ አደሮች

83

ማይጨው ጥር 6/2011 ፍርያት ኦፍላ ብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ዩኒየን የብድር መድን ዋስትና የነበረባቸውን የእዳ ጫናና ተያያዥ ችግሮች እንዳስቀረላቸው በትግራይ ደቡባዊ ዞን የኦፍላ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የወረዳው  የሕብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ ጽህፈት ቤት በበኩሉ የብድር መድን ዋስትና አገልግሎት የታለመለትን ዓላማ እያሳካ መሆኑን አስታውቋል።

የትግራይ ደቡባዊ ዞን የኦፍላ ወረዳ አንዳንድ አረሶ አደሮች ለኢትዮዽያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በዩኒየናቸው የገቡት የብድር መድን ዋስትና የእዳ ጫናቸውንና መሰል ችግሮቻቸውን አስቀርቶላቸዋል።

በወረዳው የሰሰላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዘውዴ አባዲ እንዳሉት ከእዚህ ቀደም የጤና ችግር ሲገጥማቸው ከብድርና ቁጠባ ሕብረት ሥራ ማህበር ብድር ወስደው ለመመለስ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የጤና ችግር ሲገጥማቸው በብድር የወሰዱት ገንዘብ በዩኒየኑ የሚሸፈን በመሆኑ ከስጋት እንዳዳናቸው ገልጸዋል።

የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሽሽግ ፀጋይ ከእዚህ በፊት ድንገተኛ አደጋ በሚያጋጥማቸው ጊዜ ለወሰዱት ብድር ንብረታቸውን ሸጠው ዕዳውን ለመክፈል ሲገደዱ እንደነበር ገልጸዋል።

የመድን ዋስትና አባል መሆናቸው በአደጋ ጊዜ የወሰዱትን ብድር የቁጠባና ሕብረት ሥራ ማህበሩ ስለሚሸፍንላቸው እፎይታን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

የኦፍላ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሞላ ታደሰ በበኩላቸው "የብድር መድን ዋስትና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናችን ከስጋት ነጻ አድርጎኛል" ብለዋል።

የፍርያት ኦፍላ ብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብረእግዜአብሔር ዘሩ ቀደም ሲል የነበረው የዩኒየን የብድር አሰጣጥ ስርዓት በአርሶ አደሮቹ ኑሮ ላይ ጫና ያስከትል እንደነበር አስታውሰዋል።

የመድን ዋስትና አሰራሩ ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ ተበዳሪው የጤና እክል ወይም አደጋ ሲደርስበት የወሰደው ብድር ሙሉ በሙሉ በማህበሩ እንዲሸፈን የሚያደርግ በመሆኑ አርሶ አደሩን ከስጋት ነጻ ማድረጉን ገልጸዋል።

ዩኒየኑ በተያዘው ዓመት የ10 ሚሊዮን ብር ብድር በማቅረብ 3 ሺህ 700 አርሶ አደሮችን በመጀመሪያው ዙር የብድር መድን ዋስትና ተጠቃሚ ማድረጉንም አስታውቀዋል።

የወረዳው ሕብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃፍቱ በርዎ እንዳሉት ዩኒየኑ የብድር መድን ዋስትና አገልግሎት በመጀመሩ በዚህ ዓመት ብቻ የአካል ጉዳት ላጋጠማቸው 33 አርሶ አደሮች 600 ሺህ ብር ብድር መክፈሉን ተናግረዋል።

በዩኒየኑ ሥር የተደራጁ ከ27 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በብድር መድን ዋስትና እንዲታቀፉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም