የወላይታ ሶዶ ከነማ እግር ኳስ ቡድን "የመፍረስ አደጋ ተጋርጦብኛል" አለ

78

ሶዶ ጥር 6 /  2011 የወላይታ ሶዶ ከነማ እግር ኳስ ቡድን የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠበት የወላይታ ሶዶ ከነማ እግር ኳስ ቡድን አስታወቀ፡፡

ችግሩን ለመፍታት እየሰሩ መሆናቸውን የወላይታ ሶዶ ከተማና የወላይታ ዞን አስተዳደር ገልጸዋል።

የቡድኑ ተጫዋቾችና አሰልጣኞች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ከተመሰረተ አራት ዓመታትን ያስቆጠረው ቡድን በቂ ድጋፍ ባለማግኘቱ የመፍረስ አደጋ ውስጥ ይገኛል።

በወላይታ ከተማ አስተዳደርና በወላይታ ዞን አስተዳደር ድጋፍ የተቋቋመው ቡድን ድጋፍ በማጣቱ ሊፈርስ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የወላይታ ሶዶ ከነማ እግር ኳስ ቡድን  ምክትል አሰልጣኝ አቶ ሐብታሙ ኃይሌ ለቡድኑ አባላት የደሞዝና የጥቅማ ጥቅም መብት አለመከበራቸው በተጫዋቾችም ሆነ በአሰልጣኞች ተነሳሽነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።

የምግብና የስፖርት ትጥቅ ያለመሟላት ችግር እንደገጠመውም አስረድተዋል።

ለተጫዋቾቹ የላብ መተኪያ ስለሌላቸው ተፎካካሪ ሆነው መቆየት እንዳልቻሉ አስታውቀዋል።

ቡድኑ ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥል ችግሩን መፍታት እንደሚያስፈልግ የገለጹት አቶ ሐብታሙ፣ይህ ካልሆነ ቡድኑ የመፍረስ አደጋ እንደሚገጥመው ገልጸዋል፡፡

ቡድኑ የሚንቀሳቀሰው የአካባቢው በጎ ፈቃደኞች  በሚያደርጉት ድጋፍ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በቡድኑ በአጥቂ ቦታ ተመልምሎ መጫወት ከጀመረ ሁለት ዓመታት ማስቆጠሩን የተናገረው ፈጠነ ተክለማሪያም የቡድኑ  ፈተና ከባድ መሆኑን ይናገራል።

የአካባቢው ህዝብ ለእግር ኳስ ባለው ፍቅር ቡድኑን እየደገፈ መሆኑንና በአስተዳደር አካላት ይሰጥ የነበረው ድጋፍ መቋረጡ ተስፋ እንዳስቆረጠው ተናግሯል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባየሁ ኡኩሞ ቡድኑ ያቀረበው ቅሬታ ትክክለኛ መሆኑን አምነው፣ ችግሩ የተከሰተው ከተማው በገጠመው የገንዘብ እጥረት ነው ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት ከቡድኑ ጋር ውይይት መደረጉን የጠቆሙት ኃላፊው፣ ከወላይታ ዲቻ  ስፖርት ክለብ ጋር በመነጋገር የሜዳና የስልጠና ግብዓት መፈታቱን አመልክተዋል።

የላብ መተኪያና የአበል ክፍያ በሜዳና ከሜዳ ውጭ በሚል ለማስተካከል መግባባት ላይ መደረሱን ያስታወቁት አቶ አበባየሁ፣ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የትጥቅ ግዥ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የተጫዋቾችን የምግብ አቅርቦት ችግር ለመፍታት የወላይታ ዞን አስተዳደርና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል ብለዋል።

ቡድኑ የገንዘብ አቅሙን እንዲያሳድግና ህዝባዊ መሰረቱን ለማጠናከር ተከታታይ ስራዎች እንደሚሰሩ ገልጸው፣ ከባለሀብቶችና ከተለያዩ ተቋማት ጋር ለመስራት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የወላይታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ፍሬው ሞገስ በበኩላቸው ከቡድኑ የተነሳውን ቅሬታ ለመመለስ ጉዳዩን ለዞኑ ስፖርት ምክር ቤት መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ የቡድኑን ችግር እንደሚፈታም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም