በሰቆጣ የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት በአድዋ ደግሞ የውሃ ማጠሪያ ፕሮጀክት ግንባታ መጓተት ቅሬታ ፈጥሯል

72
ሰቆጣ/አክሱም ግንቦት 20/2010 በዋህግምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሰቆጣ ከተማ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት መቸገራቸውን በከተማው አስተያየታቸውን ለኢዜአ   የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአድዋ  የተጀመረው የውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ በመጓተቱ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል። በሰቆጣ  ከተማ  ማይ የቡሊት አካባቢ  ነዋሪ ወይዘሮ ሰላማዊት ታደሰ እንዳሉት በከተማው የሚስተዋለው የውሃ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ በተለይም ባለፈው አንድ ወር የውሃ አቅርቦት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት " ሁለት ልጆቼን  በየእለቱ ጀሪካን አስይዤ ውሃ እንዲቀዱ ስለምልካቸው ትምህርታቸውን  በአግባቡ እንዳይከታተሉ አድርጓቸዋል "ብለዋል፡፡ በከተማዋ የቀበሌ ሁለት ነዋሪ አቶ አበበ ጉደታ በበኩላቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ የጉድጓድን ውሃ ለመጠጥነት ለመጠቀም መገደዳቸውን ገልጸው  በዚህም እሳቸውና ልጆቻቸው  ለበሽታ መደረጋቸውን ተናግረዋል። በየአስር  ቀኑ ልዩነት የውሃ አቅርቦቱ ይደርሳችኋል ቢባልም በተባለው ጊዜ ሊደርሳቸው እንዳልቻለ ነው ያመለከቱት፡፡ ወይዘሮ ወይዘር ካሳሁን በሰጡት አስተያየት በቂ የመጠጥ አቅርቦት ባለመኖሩ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም አሰፋ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ "ለከተማዋ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚሰጠው ጥልቅ ጉድጓድ ከተገነባ 10 ዓመታት መሆኑ የማመንጨት አቅሙ እየቀነሰ ነው "ብለዋል። በዚህም ቀደም  ጉድጓዱ በሰከንድ 15 ሊትር ይሰጥ እንደነበረ አሁን ላይ ወደ 4 ሊትር ዝቅ ማለቱን ጠቁመው የተጠቃሚው ቁጥርም ከ19 ሺህ ወደ 35 ሺህ ከፍ በማለቱ ጭምር እንደሆነ አመልክተዋል። ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት  አቅርቦቱ በፈረቃ  ለህብረተሰቡ እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰው "ተጨማሪ በአንድ ሚሊዮን 800ሺህ ብር ብር ወጪ ስምንት አነስተኛ የእጅ ጉድጓዶች በመገንባት  ለህብረተሰቡ  አገልግሎት  እንዲሰጡ  ተደርጓል "ብለዋል፡፡ የውሃ ጉድጓድ ላላቸው ግለሰቦችም በነፃ የውሃ ማከሚያ ኬሚካል በየወሩ እየተሰራጨላቸው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ የከተማዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በዘላቂነት ለመፍታትም የዲዛይን ስራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ አብረሃም ጠቁመዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ለአድዋ ከተማና አካባቢው ነዋሪ ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን በሶስት እጥፍ ያሳድጋል ተብሎ ግንባታውን የተጀመረው " የምድማር" የውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክት እስካሁን ባለመጠናቀቁ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። ከነዋሪዎቹ መካከል  አቶ ገብረመስቀል ልዑል ለኢዜአ እንዳሉት  የውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክቱ በተያዘው ዓመት መጀመሪያ ላይ ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ ቢነገረንም ግንባታው እስካሁን አላለቀም። "በወቅቱ ባለመጠናቀቁ በተደጋጋሚ የህበረተሰቡ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል" ያሉት አቶ ገብረመስቀል፣በአድዋ ከተማ ተደጋጋሚ የመጠጥ የውሃ መቆራራጥ እያጋጠመ መቸገራቸውን ገልጸዋል። በአካባቢው በቂ የውሃ ሃብት እያለ የማጣሪያ ፕሮጀክቱ ባለመጠናቀቁ  ውሃ በፈረቃ ተደርጉ ውሀ  የሚያገኙት እስከ አራት ቀናት ቆይቶ ነው፡፡ ችግሩን እየበረታ በመምጣቱ  ሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያመቻችላቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ በከተማው በተፈጠረው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መቆራረጥና እጥረት ምክንያት መቸገራቸውን የተናገሩት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አወጣሽ ገብረኪዳን ናቸው። አሁንም የሚመለከተው አካል የተጀመረውን ፕሮጀክት አጠናቆ ተገቢ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ሰጥቶ መሰራት እንዳለበትም አመልከተዋል፡፡ የዓድዋ ከተማ ውሃና ፍሰሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ገብረእግዚአብሔር ስለጉዳዩ ተይቀው በሰጡት ምላሽ "የፕሮጀክቱ ሲቪል ስራዎች ተጠናቆ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ባለመጠናቀቁ ተጓቷል" ብለዋል። የውሃ ማሰራጫ ቱቦ የመዘርጋትና በከተማው አስተዳደር አቅም የሚከናወኑ ሌሎች ስራዎችን መጠናቀቀቸውንም ገልጸዋል። የውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክቱ አካል የሆነው የኤሌክትሮሜካኒካል ስራው በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያዎች ወራት ላይ ተጠናቅቆ አገልገሎት መስጠት እንደሚጀምር ከትግራይ ክልል ውሃ ሃብት ቢሮ እንደተገለጻላቸው ተናግረዋል። የክልሉ ውሃ ሃብት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፍትዊ ግደይ በበኩላቸው ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ የኤልክትሮ መካኒካል እቃዎች በሃገር ውስጥ ገበያ እንደሌሉና ከውጭ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የእቃዎቹ የግዥ ሂደት እንደተጀመረና የገቢ እቃዎች በዶላር ዋጋ ጭማሪ ምክንያት በተፈለገው ጊዜ ሊገኝ አለመቻሉንም ጠቁመዋል። " በዚህ ምክንያትም ፕሮጀክቱ በዚህ ጊዜ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ነው" ያሉት ኃላፊው፣ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በመደበው 300 ሚሊዮን ብር ወጪ ነው እየተገነባ የሚገኘው። እስከ አሁን ከፕሮጀክቱ አጠቃላይ ግንባታ 75 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በተያዘው በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ የኢዜአ ሪፖርተር ዘግቦ እንደነበር ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም