ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ለስደተኞች የምታደርገውን ድጋፍ የማገዝ ፍላጎት አለው

75

አዲስ አበባ የካቲት 5/2011 ኢትዮጵያ ለስደተኞች የምታደርገውን ድጋፍ ጫና ለማቃለል ለአገሪቱ ዜጎች በሚጠቅም የዘላቂ ልማት ሥራዎች ላይ እገዛ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው የመንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ አስታወቁ።

የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፕ ግራንዴ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ  ጋር ዛሬ በጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ከውይይቱ በኋላ የኮሚሽኑ ኃላፊ ፊሊፕ ግራንዴ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ለስደተኞች እያደረገች ላለው  አቀባበልና ድጋፍ  ምስጋና ችረዋል።

ኢትዮጵያ ዘጠኝ መቶ ሺህ ለሚጠጉ የኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሌሎች ስደተኞች መጠለያ በመሆን የድርጅቱ ግንባር ቀደም አጋር መሆኗን ኃላፊው ገልፀዋል።

በተለይ ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ጥቅሞችን ጨምሮ የስደተኞችን ሰብአዊ መብት ለማስጠበቅ በቅርቡ ያፀደቀችውን የስደተኞች ጉዳይ አዋጅን በአድናቆት  አንስተዋል።   

አክለውም የስደተኞችን ሰብዓዊ ድጋፍ ከማረጋገጥ ባሻገር የኢትዮጵያዊያን  ዘላቂ ልማት የመደገፍ ፍላጎት በሚመሩት ዓለም አቀፍ ድርጅት በበኩሉ እንዳለ ተናግረዋል።

አገሪቱ እያስተናገደቻቸው ባሉት ስደተኞች ምክንያት ሊፈጠርባት የሚችለውን ጫና ለማቃለል ኮሚሽኑ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያእንደሚያደርግ ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀጠናው ሰላም ለማምጣት እየሰሩት ያለው ጠንካራ ሥራ ፍሬ አፍርቶ በርካታ ስደተኞች ወደ የአገራቸው እንደሚመለሱ ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ተሻሽሎ የወጣው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ የስደተኞቹን ህይወት ከማሻሻል በተጨማሪ ለአገሪቱም ከፍተኛ ኃብት ለማመንጨት የሚጠቅም መሆኑም አብራርተዋል።

ለአብነትም በደቡብ ሱዳን እየተሻሻለ የመጣውን ሰላም በዋቢነት በማንሳት ስደተኞችን ወደየመጡባቸው አገራት ለመመለስ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም አክለዋል።

ቀጠናው የበለጠ ሰላም ሆኖ የስደተኞች ቁጥር እንደሚቀንስ ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም