በጌዴኦ ዞን የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ መጠናከር እንዳለበት ተጠቆመ

79

ዲላ  የካቲት 5/2011 በጌዴኦ ዞን በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተጠቆመ ፡፡

የጌዴኦ ዞን የ2011 የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በዲላ ዙሪያ ወረዳ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል ፡፡

በወረዳው ሺገዶ ቀበሌ በተዘጋጀው ይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንደተናገሩት በክልሉ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በተከናወነባቸው ስምንት ዓመታት በርካታ ሥነ-አካላዊና ሥነ-ሕይወታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡

በተቀናጀ የተፈሰስ ልማቱ እስካሁን ካጠቃላይ የክልሉ መሬት 38 በመቶ የሚሆነው በሥነ አካላዊ ሥራ መሸፈኑን የተናገሩት ኃላፊው "የልማት ሥራው ሲጀመር 19 ከመቶ የነበረውን የክልሉን የደን ሽፋን በአሁኑ ወቅት ወደ 22 ነጥብ 5 ማሳደግ ተችሏል" ብለዋል፡፡

በዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የምርትና ምርታማነት ማሻሻያ ሥራዎች በትኩረት እየተሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በተለይ ቡና አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ያረጁና ምርት የማይሰጡ ቡናዎች ጉንደላና ነቀላ፣ የመተከያ ጉድጓድ ቁፋሮ፣ የማሳ ውስጥ እርጥበት እቀባ ሥራ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጀትና ሌሎች የቡና ልማት ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆናቸውን ነው የተናገሩት ፡፡

"ጌዴአና ቡና የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው" ያሉት አቶ ጥላሁን የአርሶ አደሩ የኢኮኖሚ ዋስትና የሆነውንና ዞኑ በዓለም ደረጃ የሚታወቅበትን ቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

የጌዴኦ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው የዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የዞኑ ህዝብ በዋናነት የሚያለማውን የቡና ምርትና ምርታማነት መጨመር የሚያስችሉ ተግባራት ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ገዙ እንዳሉት የተፋሰስ ሥራው የጌዴኦ ህዝብ ለዘመናት ሲጠቀምበት የቆየውን ቡና፣ እንሰትና ዛፍን በአንድ ላይ በመትከል ምርትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን አስተሳስሮ በማስቀጠል የሚታወቅበትን ጥምር ግብርና ዘዴን ጠብቆ ለማቆየት ያግዛል።

የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተገኝ ታደሰ በበኩላቸው በልማቱ 339 ሺህ 238 አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉና ልማቱም 133 ንዑስ ተፋሰሶች መሰረት በማድረግ በ39 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እንደሚከናወን አብራርተዋል ፡፡

"ከዚህ ቀደም በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረጋቸው የጠፉ ምንጮችን መልሶ ማጎልበት፣ የእንስሳት መኖን በስፋት ማምረት እንዲሁም የአፈር መከላትን መከላከልና በማሳ ውስጥ እርጥበትን አቅቦ ማቆየት ተችሏል" ብለዋል፡፡

ዞኑ ካለው 134 ሺህ 700 ሄክታር መሬት ውስጥ 51 በመቶ የሚሆነው የተሸፈነው በቡና ተክል መሆኑን ጠቁመው የዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከወትሮው በተለየ መልኩ በቡና ምርትና ምርታማነት ማሻሻያ ተግባራት ላይ ማተኮሩን አስረድተዋል ፡፡

በዞኑ ካለው 68 ሺህ ሄክታር በላይ የቡና ተክል በ51 ሺህ ሄክታር ላይ የሚገኘው ምርት እየሰጠ ቢሆንም ከዚህ ውስጥ 32 ሺህ ሄክታር የሚሆነው እድሜው ከ20 ዓመት በላይ የሆነ፣ ያረጀና ምርታማነቱን እየቀነሰ የመጣ መሆኑን አቶ ተገኝ ተናግረዋል ፡፡

እንደኃላፊው ገለጻ ያረጁ ቡናዎችን መጎንደል፣ ምርት የማይሰጡትን ነቅሎ በመተካት እንዲሁም ሌሎች የምርታማነት ማሻሻያ ፓኬጆችን በመተግበር በአማካይ በሄክታር 9 ነጥብ 4 ኩንታል የሆነውን ዞናዊ የቡና ምርት ወደ 13 ኩንታል ለማሳደግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው፡፡

በዘንድሮው የተፈጥሮ ህብት ጥበቃ ስራም ከሰባት ሺህ 352 ሄክታር ላይ የቡና ጉንደላና 8 ሺህ ሄክታር ላይ ደግሞ የነቀላ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል ፡፡

የቡና ችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት እንዲሁም በማሳ ውስጥ የሚከናወኑ የአፈር ጥበቃና የእርጥበት እቀባ ሥራዎችም የተፋሰስ ሥራው አካል መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የተፋሰስ ልማት ሥራ በደቦ ሲሰሩ ከተገኙ የሺገዶ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ሽብሩ በራቆ ባለፉት ዓመታት ባከናወኗቸው ተግባራት የአካባቢያቸው አረንጓዴነት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል ፡፡

"አምና በዚህ ወቅት የጎነደልኳቸው ያረጁ ቡናዎች አቆጥቁጠው ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛሉ" ያሉት አርሶ አደሩ ዘንድሮ በርከት ያሉ ቡናዎችን በደቦ ለመጎንደል መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል ፡፡

በሰሯቸው የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የማሳቸውን እርጥበት በመጠበቃቸውና የሚያዘጋጁትን ተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቅመው በጓራቸው የፈለጉትን ምርት ማምረት በመቻላቸው አብዛኛው የምግብ ፍጆታቸውን ከማሳቸው እንደሚያገኙ የተናገሩት ደግሞ ሴት አርሶ አደር አስራት ተሸመ ናቸው፡፡

የተፋሰስ ልማት ሥራው እስኪጠናቀቅ ድረስ በልማት ቡድናቸው አማካይነት ትገተው እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡ በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ በተዘጋጀ የ2011 የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ ማብሰሪያ ምርሀ-ግብር ላይ የፌዴራል ባለሙያዎች፣ የደቡብ ክልልና የጌዴኦ ዞን አመራር አካላት፣ የባህልና የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም የሺገዶ ቀበሌ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም