በደቡብ ክልል የሆስፒታሎች የሥራ አመራር ቦርድን በአዲስ መልክ ለማደራጀት እየተሰራ ነው

287

ሀዋሳ የካቲት 5/2011 በሆስፒታሎች የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡ መመለስ እንዲቻል የሆስፒታሎች የሥራ አመራር ቦርድን በአዲስ መልክ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ሚኒስቴሩ የሆስፒታሎችን ሥራ አመራር ቦርድ በአዲስ መልክ ለማደራጀት ባዘጋጀው ረቂቅ የማስፈጸሚያ ማንዋል ላይ በሀዋሳ ከተማ ሲሰጥ የነበረው የሁለት ቀን ስልጠና ተጠናቋል።

በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሀባስ ሀሰን ለኢዜአ እንደገለጹት በሀገሪቱ የሚገኙ ሆስፒታሎች በሥራ አመራር ቦርድ እንዲመሩ ማድረግ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

ከአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከበጀት አጠቃቀም ከመድኃኒትና ክህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ቅሬታዎች በቦርድ ታይቶ ውሳኔ መስጠት በመቻሉ ለውጡ እየተመዘገበ መምጣቱን ተናግረዋል።

በአንዳንድ ሆስፒታሎች እየተዳከመ የመጣውን የቦርድ አመራር ለማጠናከርና የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ማስተካከል እንዲቻል የሆስፒታል ሥራ አመራር ቦርድ የማስፈጸሚያ ማንዋል ረቂቅ ሰነድ ላይ ስልጠናው መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

ማኑዋሉ አሰራሩን ወጥ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።

በአምስት ዓመት የጤናው ሴክተር ዕቅድ በዋናነት እምርታዊ ለውጥ ይመጣባቸዋል ተብለው ከተለዩ ጉዳዮች አንዱ አጠቃላይ የተቋማት አመራርን ማሻሻል መሆኑንም ተናግረዋል።

በሃዋሳ ከተማ የአዳሬ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅና በመድረኩ የተሳተፉት አቶ ሙጣሻ ብርሀኑ እንዳሉት “የአዳሬ ሆስፒታል የአመራር ቦርድ ከህብረሰተቡ ጋር ተቀራርቦ እየሰራ ይገኛል”።

ሆስፒታሉ በየሦስት ወሩ ህዝባዊ ውይይት እንደሚያዘጋጅና በውይይቱ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን መሰረት ያደረገ የማስተካከያ ሥራዎችን  ስለሚሰራ በአሁኑ ወቅት የአገልግሎት አሰጣጡ ግልጽ፣ ፍትሀዊና ቀልጣፋ መሆኑን ተናግረዋል።

” ቦርዱ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለከተማው ከንቲባ መሆኑንና የህብረተሰብ ተወካዮችም የሚገኙበት በመሆኑ ለሆስፒታሉ አገልግሎት መሻሻል ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው”ብለዋል።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የወራቤ ሆስፒታል ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዘይኔ ቢልካ በበኩላቸው በሆስፒታሉ የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን ለይቶ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና በጳውሎስ ሆስፒታል እገዛ ለማሟላት መቻሉን ተናግረዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ የስልጤ ልማት ማህበር ለሆስፒታሉ የተለያዩ መሳሪያዎችን በልገሳ መደገፉን ነው የተናገሩት።

የሕክምና ባለሙያዎችንና ሌሎች የሆስፒታሉ ሠራተኞችን የማበረታቻ ሽልማትና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ መደረጉም ሆስፒታሉን በክልሉ ቀዳሚ ለማድረግ ማስቻሉን ገልጸዋል።

“ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የሚገኙ ሆስፒታሎች በሥራ አመራር ቦርድ እንዲመሩ ተደርጓል” ያሉት ደግሞ የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ ናቸው።

በእዚህም ከፍተኛ ለውጥና መሻሻል መምጣቱንና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ክፍተቶች መቀነሳቸውን ጠቁመው ከበጀት አመዳደብ ጋር በተያያዘ አሁንም የሚስተዋሉ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት በሃዋሳ ከተማ ሲካሄድ በነበረው ስልጠና ላይ በደቡብ ክልል የሚገኙ ሆስፒታሎች ሥራ አስኪያጆች፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና የሥራ አመራር ቦርድ ኃላፊዎች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።