አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ማጠናከር ትፈልጋለች

659

አዲስ አበባ  የካቲት 5/2011 የአሜሪካ መንግስት ከአፍሪካ አገራት ጋር ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የማሳደግ ቁርጠኛ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

የአሜሪካ -አፍሪካ  የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ለሁለት ቀናት አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል። 

‘ኮርፕሬት ካውንስል ኦን አፍሪካ’ የተሰኘው የአሜሪካ መንግስታዊ ተቋም ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ፎረሙ ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ባለኃብቶችና የመንግስት ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በአፍሪካ የምጣኔ ኃብታዊ ልማት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ልዩ ረዳት የሆኑት ሲሪል ሳርቶር በፎረሙ ላይ እንደተናገሩት አሜሪካ ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር የማሳደግ ፍላጎትና ቁርጠኝነት አላት ብለዋል።

የፎረሙ ዓላማም ይህንን የአሜሪካ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ግንኙነቱ በሚጠናከርበት መንገድ ላይ መወያየት እንደሆነ አንስተዋል።

በአፍሪካ ህብረት የአሜሪካ አምባሳደር ሜሪ ቤት ሊዩናርድ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነቱ ገቢራዊ ሲሆን አሜሪካና ሌሎች አገራት በአፍሪካ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ እንዲንቀሳቀሱ የበለጠ እድል ይፈጠራል ሲሉ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የንግድና ኢንዱስትሪ ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋ እንደገለፁት ፎረሙ በአፍሪካ የግሉን ዘርፍ ኢንቨሰትመንት ለማሳደግ መከናወን ስለሚኖርባቸው ተግባራት መግባባት ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል። 

አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ይህም የግሉ ዘርፍ ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴን ለማሳደግ የሚያግዝ እንደሆነም ተናግረዋል።

የቀጠናው እውን መሆን ባለኃብቶችም በአፍሪካ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ የሚያበረታታ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የአሜሪካ መንግስት ከአፍሪካ ጋር ያለውን የንግድ ትስስር ለማጠናከር ያሳየውን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል።