ኮሚሽኑ ለአዲሱ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመስጠት ኃላፊነት አለበት-ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

606

አዲሰ አበባ የካቲት 5/2011 የእርቀ-ሰላም ኮሚሽን ለአዲሱ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመስጠት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ለኮሚሽኑ አባላት የትውውቅና የስራ መመሪያ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሰጥቷል።

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንደተናገሩት የኮሚሽኑ አባላት በአገሪቱ የተከሰቱና የሚከሰቱ የግለሰብና የቡድን ግጭቶችን በገለልተኛነት ለመፍታት ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

አገሪቱ ያላትን መልካም እሴቶች በመጠቀም ለትውልድ የሚሻገር ሰላምና አንድነት ለማምጣት የኮሚሽኑ አባላት የተሰጣቸውን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።

“በአገሪቱ በትውልዶች መሀከል በመወቃቀስና አገርን አፍርሶ በመስራት ብዙ ጊዜ ባክኗል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ እንዳይደገም የተቋቋመው ኮሚሽን ትልቅ ኃላፊነት እንደተጣለበት አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ኢትዮጵያን ለመቀየር ትልቅ ዕድል እንዳለውና ስራውን በትዕግስትና በጥበብ በመወጣት የተጀመረውን ለውጥና የአገሪቱን መልካም ገጽታ ማጎልበት ይገባል ብለዋል።

መንግስት አስፈላጊ ግብዓትና ስልጠናዎች እንዲሁም ለመነሻ የሚሆኑ ጽሁፎችን ከሟሟላት ባለፈ ኮሚሽኑ በሚያካሂደው የእርቀ-ሰላም ስራ ጣልቃ አይገባም ብለዋል።

ኮሚሽኑ ስራውን ነገ በይፋ እንደሚጀምርና ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የስራ ዘመን እንዳለው ታውቋል።

ኮሚሽኑ ከኃይማኖት ተቋማት፣ ከፖለቲከኞች፣ ከምሁራን፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከአባ ገዳዎች፣ ከታዋቂ ሰዎች እና ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የተውጣጡ 41 አባላት አሉት።

አባላቱ የተሰጣቸውን አገራዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ጥረት እንደሚያደርጉ የገለጹ ሲሆን የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።

ዶክተር ብርሃኑ ደሬሳ በሰጡት አስተያየት የዛሬ 50 እና 100 ዓመትም ጥፋቶችን እያወራን ከምንሄድ የእሱን ፋይል ዘግተን የሚመጣው ትውልድ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲገባ ከእኛ ብዙ ይጠበቃል ፤ተቃዋሚም እንሁን የሃይማኖት አባት ሰላም አስፈላጊ  ነው ብለዋል።”

”ለእኛ ከሊቃውንቱ ከምሁራኑ ጋር አብሮ መዋሉ ሰላምን ለማምጣት ትልቅ ሚና አለው ትምህርትም ለማግኘት ይረዳል። እንደ ግልም አገራዊ ግዴታን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ የዜግነትም ግዴታም አለብን ብዬ አምናለሁ።” ያሉት ደግሞ ብጹዕ አብነ አብርሃም ናቸው፡፡

ዶክተር ምህረት ደበበ እንዳሉት  “ብዙ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ስራ ሲቋቋም በዕድሜያቸው የታችኛው ክፍል የሆኑ ሰዎች አይወከሉም። በዚህ ኮሚሽን ግን ዕድሜአቸው ወጣት የሆኑ ሰዎች መወከላቸው ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። እርቅ ከሽምግልና ጋር ቢያያዝም ጠብ ከወጣትነት ጋር ስለሚያያዝ አብሮ ሁለቱም መኖሩ ጥሩ ነው። ወጣቶችም የራሳቸው ሃሳብና ጥበብ ስላላቸው ይህ ደግሞ እዚህ ውስጥ መኖሩ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ”። 

ብሄራዊ የእርቀ-ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ታህሳስ 16 ቀን 2011 ዓም የጸደቀ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ አድርገዋል።