የምስራቅ አፍሪካ አገሮች አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን በማጽደቅ ቀዳሚ መሆናቸው ተገለጸ

123

አዲስ አበባ የካቲት 5/2011 የምስራቅ አፍሪካ አገሮች አህጉራዊ ነፃ የንግድ አካባቢ ለመፍጠር የተደረሰውን ስምምነት በፍጥነት በማጽደቅ ቀዳሚ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ አስታወቁ።

አህጉራዊ ነፃ የንግድ አካባቢ ለመፍጠር የተደረሰውን ስምምነት ኢትዮጵያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ያጸደቀች ሲሆን በቅርቡም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል ታጸድቃለች ተብሎ ይጠበቃል።

እስከ አሁን በምስራቅ አፍሪካ ካሉ አገሮች ኢትዮጵያ ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ሩዋንዳ ስምምነቱን ያጸደቁ ሲሆን ጅቡቲም እንደምታጸድቅ የኮሚሽኑ ዋና ፀሐፊ ቬራ ሶንግዌ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ስምምነቱን በማጽደቅ በኩል በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ሶንግዌ ''ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በቅርቡ ያጸድቃሉ የሚል ተስፋ አለን ብለዋል።

እስካሁን 18 አገሮች ያጸደቁ ሲሆን ውጤታማ ለመሆን 22 አገሮች ማጽደቅ አለባቸው። "ከኅብረቱ ጉባዔ በኋላ ቁጥሩ 22 ይደርሳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ፤ ይህ ካልሆነ ግን እርግጠኛ ነኝ ሰኔ ላይ ስምምነቱን ያጸደቁ አገሮች ቁጥር 22 ይደርሳሉ'' ብለዋል። 

አንድ አህጉራዊ ገበያ እና ነጻ የሰዎች ዝውውር ስምምነት ይፋ የሆነው መጋቢት 2010 ዓም በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ጉባኤ ነበር።

ስምምነቱ ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ 18 አገሮች ያጸደቁት ቢሆንም በተቀመጠው አሰራር መሠረት 22 አባል አገሮች ማጽደቅ አለባቸው።

የአፍሪካ ኅብረት በአጀንዳ 2063 ከያዛቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ የአፍሪካ ነጻ ገበያ አካባቢና ነጻ የሰዎች ዝውውር አንዱ ነው።

በዚህ ረገድ "ዘላቂ አስተማማኝ መፍትሄ በኃይል ለሚፈናቀሉ አፍሪካዊያን፣ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች" በሚለው የ32ኛ የኅብረቱ መሪዎች ጉባኤ መሪ ቃል መሠረት የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከአፍሪካ ኅብረት ጋር እየሰራ መሆኑን ቬራ ሶንግዌ አብራርተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከስደተኞች ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቅንጅት ስራ ማጠናቀቁን የገለጹት ዋና ፀሐፊዋ ''ለአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ በማድረግ ካገኘነው ምስጋና ይልቅ ተጠቃሚዎች ነን'' ብለዋል።

በርካታ የአፍሪካ አገሮች ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቅንጅት ስምምነት መፈረማቸውን ገልጸዋል። 

''ለአፍሪካ አገሮች ስጋት የሆነው የራሳቸው ስደተኞች ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት 28 አገሮች የካምፓላ ስምምነትን በመቀበላቸው አፍሪካ በአገር ውስጥ ተፈናቃይ ሰዎችና ስደተኞች ጉዳይ ተምሳሌት እንደምትሆን ተስፋ አለኝ'' ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ 14 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንዳሉ የገለጹት ዋና ፀሐፊዋ ለስደተኞቹ እንክብካቤ ለማድረግ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል።               

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም