ተቋማት በስርዓተ ፆታ አካታችነት ላይ አርአያነት ያለው ተግባር ሊያከናውኑ እንደሚገባ ተገለፀ

125
አዳማ ሚያዚያ 26/2010 የፐብሊክ  ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ተጠሪ ተቋማት በስርዓተ ፆታ አካታችነት ላይ አርአያነት ያለው ተግባር ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ፡፡ በስርዓተ ፆታ አካታችነት ዙሪያ ያተኮረ አገር አቀፍ የስልጠና መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል ። የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር የሰው ሀብት ስራ አመራር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ስልጠናውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተጀመረው አገራዊ ርብርብ በሁሉም ዘርፍ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ከተመዘገቡ ውጤቶች መካከልም የሴቶችን ንብረት የማፍራት ፣ የማስተዳደር ፣ የመቆጣጠርና የማስተላለፍ መብታቸው መከበሩ ፣ የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ እያደገ መምጣቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ የጤና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የእናቶችና ህፃናት ሞት መቀነ መቻሉ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና   ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየቀነሱ መምጣታቸውንና የሴቶች የውሳኔ ሰጪነት እያደገ መምጣቱንም አመላክተዋል፡፡ ''ከሚጠበቀውና ከሚፈለገው ውጤት አኳያ ገና ብዙ መስራት ይጠበቃል'' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በአፈፃፀም ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላት በሁሉም ዘርፎች የስርዓተ ፆታን በማካተት አገራዊ ግስጋሴውን ሙሉ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል ። በተለይ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ተጠሪ ተቋማት የስርዓተ ፆታን የእቅዳቸው አካል አድርገው በመተግበር አርአያነት ያለው ተግባር የመፈፀም ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል ። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስርዓተ ፆታ ጉዳይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ንግስት ጌታቸው በበኩላቸው የስልጠናው ዓላማ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን በፐብሊክ ሰርቪሱ በማረጋገጥ እንደአገር ለተቀመጠው ራእይ ተደማሪ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ነው ። በስልጠናው ላይ ከፌዴራል የፐብሊክ ሰርቪስ ተጠሪ ተቋማት፣ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት የበላይ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል። ተሳታፊዎቹ በሁለት ቀናት ቆይታቸው በስርዓተ ፆታ አካታችነት ምንነትና በስርዓተ ፆታ ማካተቻ መመሪያ ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጡ እንደሚደረግ ወይዘሮ ንግስት ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም