በትግራይ ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የቦክስ ስፖርት ውድድር ተጀመረ

380

መቀሌ የካቲት 5/2011 በትግራይ ክልል ለሃያ ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የቦክስ ስፖርት ውድድር ተጀመረ።

ውድድሩ ዳግም በመጀመሩ ደስተኛ መሆናቸውን የቦክስ ስፖርት ተወዳዳሪዎች ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የቦክስ ፌዴሬሽን አስተባባሪ አቶ ጥላሁን ተክለ እንዳሉት የቦክስ ስፖርት ውድድር ለ20 ዓመታት ያህል ተቋርጦ በመቆየቱ በዘርፉ ተተኪዎችን ማፍራት አልተቻለም።

በአራተኛው መላው የትግራይ ክልል የትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር ላይ 120 የፕሮጀክት ሰልጣኝ ቦክሰኞች የተሳተፉበት የቦክስ ስፖርት ውድድር እንዲካሄድ መደረጉን አመልክተዋል።

የቦክስ ስፖርታዊ ውድድርን ይበልጥ ለማጠናከር በክልሉ በሽሬ እንዳስላሴ፣ በአዲግራት፣ በአድዋና መቀሌ ከተሞች ከ15 ዓመት ዕድሜ በታች ለሆኑ 200 የፕሮጀክት ሰልጣኝ ታዳጊ ህጻናት የቦክስ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም አስረድተዋል።

በበትግራይ ደቡባዊ ዞን የአላማጣ ከተማ የቦክስ ተወዳዳሪ ታደሰ ግርማይ በበኩሉ፣ “በክልሉ ተቋርጦ የነበረው የቦክስ ስፖርት መጀመሩ እንደእሱ ከ15 ዓመት ዕደሜ በታች የሆኑ ታዳጊ ሕጻናት በፕሮጀክት ታቅፈው እንዲሰለጥኑ እድል ይፈጥራል” ብሏል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉንና የአገሩን ስም ለማስጠራት የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑንም ተናግሯል።

በቦክስ ስፖርት ለመወዳደር የከተማው መስተዳደር የገንዘብና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን የተናገረችው ደግሞ የዓድዋ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሳምራዊት ንጉሰ ናት።

“የቦክስ ስፖርት የድብድብና ጥላቻ ሳይሆን ከሌሎች የስፖርት ዓይነቶች የበለጠ ቀልብ የሚስብ በመሆኑ በቦክስ ስፖርት ለመቀጠል እቅድ አለኝ” ስትልም ተናግራለች።