በሰሜን ሸዋ አርሶ አደሮች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እያከናወኑ ነው

893

ፍቼ የካቲት 5/2011 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች በአርሶ አደሮች ተሳትፎ የተጠናከረ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ግርማ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት አርሶ አደሮቹ አካባቢያቸውን በማልማት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲችሉ ለአስር ቀናት በግንባር ቀደም አርሶ አደሮችና በባለሙያዎች የአመለካከትና የክህሎት ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

በልማቱ  በዞኑ 13 ወረዳ የሚገኙ ከ331 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች በቡድን በመሆን አካባቢያቸውን እያለሙ መሆኑን እና እስካሁን ባደረጉት እንቅስቃሴም ከ15 ሺህ ኪሎ ሜትር በሚበልጥ መሬት ላይ የእርከንና ክትር ስራ ማከናወናቸውን አመልክተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በ200 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የድንጋይና አፈር እርከን ሥራ፣ መለስተኛ ወንዞችን የመጥለፍ፣ ምንጮችን የማጎልበትና እርጥበትን የሚስቡ ሥራዎችን በአርሶ አደሮቹ ጉልበት ለመስራት መታቀዱን ተናግርዋል።

ለሥራው ውጤታማነት ከ135 ሺህ የሚበልጡ የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች በየቀበሌው መሰራጨታቸውንም አስረድተዋል ።

አስተባባሪው እንዳሉት ባለፈው ዓመት በፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራው ተቀዛቅዞ የነበረ ቢሆንም ከ21ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ የድንጋይና አፈር እርከን፣ የምንጭ ማጎልበትና የደን ተከላ ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል ።

በዞኑ በአሁኑ ወቅትም በዞኑ 450 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በተለያየ መንገድ ተራቁቶ ለአደጋ የተጋለጠ መሆኑንም  አመልክተዋል።

የተጎዳው መሬት በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት መልሶ እንዲያገግም ከአርሶ አደሮች፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ዕቅድ ወጥቶ እየተሰራ መሆንንም ተናግረዋል።

በኩዩ ወረዳ ቄሬንሳ ቀበሌ በልማት ስራው በመሳተፍ ላይ ካሉት አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሙሉጌታ ቦደና በሰጡት አስተያየት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራውን ጠቀሜታ በመረዳታቸው የልማት ስራውን በተነሳሽነት እያከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከባለሙያዎች ያገኙት የተግባርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የአካባቢያቸውን ለምነት ለመመለስና ከድህነት ለመላቀቅ ለሚያደርጉት ጥረት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

በያያ ጉለሌ ቃጥላ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ግንባር ቀደም አርሶ አደር ሁሪሳ ጉታ በበኩላቸው እርሳቸውን ጨምሮ የአካባቢያቸው ህብረተሰብ የአካባቢውን ልምላሜና ምርታማነት ለመመለስ የልማት ስራውን እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከጥር ወር አጋማሽ ጨምሮ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን አጠናክረው መቀጠላቸውን የገለጹት ደግሞ በግራር ጃርሶ ወረዳ ጊኖቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ውበቱ አንዳርጌ ናቸው።

በእዚህም እርጥበትንና የአፈር ለምነትን የሚጨምሩ አሰራሮችን በማከል የልማት ሥራውን በጋራ እያከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።