በአነስተኛ መስኖ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስተካከል የሚያግዝ ሰነድ እየተዘጋጀ ነው

71

አዲስ አበባ የካቲት 5/2011በኢትዮጵያ በአነስተኛ መስኖ ላይ የሚስተዋለውን የዲዛይን፣ የፕሮጀክቶች መጓተትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግር ለማስወገድ የሚያግዝ ስትራቴጂክ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሰነዱ በዚህ ዓመት ወደ ትግበራ እንደሚገባና በመስኖ ስራ ዲዛይን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችና የፕሮጀክቶች መጓተትን ያስቀራል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ኮንትራት አስተዳደርና ሌሎች በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የሚያግዝ እንደሆነም ነው ሚኒስቴሩ የገለፀው።

በሚኒስቴሩ የአነስተኛ መስኖ ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ኤሊያስ አወል ለኢዜአ እንዳሉት ከመስኖ ልማት ጥናት አንስቶ እስከ ኮንትራት አስተዳደር ድረስ ያሉትን ችግሮች የሚፈታ ሰነድ ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው።

አሁን ባለው ሁኔታ በአገሪቱ እየተገነቡ ያሉትና መጠናቀቅ የነበረባቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች ግንባታ አፈጻፀም ከ50 እስከ 60 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልፀው የስራ ተቋራጮች አቅም ማነስ፣ የመንግስት ክትትልና ቁጥጥር ዝቅተኛ መሆን ለፕሮጀክቶቹ መጓተት ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሰነዱ ተጠናቆ ተግባራዊ ሲሆን በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙትን የመስኖ ልማት ስራዎች አፈፃፀም ችግር ይፈታል ነው ያሉት። 

ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም፣ የመሬት ለምነትና መስኖን በቴክኖሎጂ የሚያግዝ ስትራቴጂን ያካተተው ሰነድ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ህትመት መግባቱንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

ሰነዱ ታትሞ ከተጠናቀቀ በኋላ ለባለሙያዎች እና ለአርሶ አደሮች ስልጠና በመስጠት በየደረጃው የሚከፋፈል ይሆናል ብለዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ አሁን ባለው የቴክኖሎጂ፣ የውሃ አቅርቦትና የገንዘብ አቅም ተጨባጭ ሁኔታ በመስኖ መልማት የሚችል ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት አለ።

በቀጣይም እስከ አምስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት መልማት እንደሚችል ነው ከሚኒስቴሩ የተገኘ መረጃ የሚያመለክተው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም