የአፍሪካ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ የአየር መንገዶችን ተጠቃሚ ያደርጋል-ግርማ ዋቄ

91

አዲስ አበባ የካቲት 5/2011የአፍሪካ ህብረት ባለፈው ዓመት ይፋ ያደረገው አህጉራዊ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ አየር መንገዶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ግርማ ዋቄ ተናገሩ።

ኢዜአ በአህጉራዊ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ዙሪያ ያነጋገራቸው አቶ ግርማ እንዳሉት፤ የመገናኛ ዘዴው ውስን በሆነበት የአፍሪካ አህጉር የአየር ትራንስፖርት መስፋፋት የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

የአየር ትራንስፖርት ሊበላሹ የሚችሉ፣ ውድ የሆኑና ከቦታ ቦታ በቀላሉ ሊንቀሳቀሱ የማይችሉ ሸቀጦችን ለማጓጓዝ ቀዳሚ ምርጫ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ግርማ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ ረገድ ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ የአበባ ንግድ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ያበቃው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መኖር እንደሆነ ገልጸው ስጋን ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገሮች በማድረስ ለስጋ ምርት የወጪ ንግድ ማደግ የበኩሉን ማበርከቱንም ገልጸዋል።

የአየር ትራንስፖርት መስፋፋት ለንግድ ዕድገት ዋነኛ መሳሪያ እንደሆነ የገለጹት አቶ ግርማ የአየር ትራንስፖርት በአገሮችና ህዝቦች መካከል የተሻለ መተሳሰር እንዲፈጠር የሚያደርግ ቀዳሚ አማራጭ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ይፋ ያደረገው አህጉራዊ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ አገሮች በሮቻቸውን ለአፍሪካ አየር መንገዶች ክፍት እንዲያደርጉ የሚያስችል በመሆኑ ትልቅ ጥቅም የሚኖረው እርምጃ ነው በማለት ነው የገለጹት።

አህጉራዊ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሁሉም የአፍሪካ አገሮች ያለአንዳች ማዕቀብ ሊሰራ የሚያስችለው እንደሚሆንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጠንካራ በመሆኑ ብዙ ቦታዎች የመግባት ዕድል ቢኖረውም ያለማዕቀብ መግባት መቻሉ ተጠቃሚ የሚያደርገው እንደሆነ ገልጸዋል።

በአህጉራዊ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ሁሉም የአፍሪካ አየር መንገዶች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደሚኖርም ጠቁመዋል።

አህጉራዊ የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ካሉት ጠቀሜታዎች መካከል የአፍሪካ አገሮች አየር መንገዶችን ማስተሳሰር፣ ተመጣጣኝ የአገልግሎት ክፍያ፣ ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር፣ አፍሪካዊያንን ማቀራረብ፣ ጊዜ መቆጠብ፣ የእርስ በርስ ንግድን ማሻሻል፣ ቱሪዝምን ማስፋፋትና የአየር መንገዶች ማደግና መስፋፋት ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም