32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ተጠናቀቀ

124

አዲስ አበባ የካቲት 4/2011 ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት ሲካሄደ የቆየው 32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክሮ መግባባት ላይ በመድረስ ዛሬ ተጠናቋል።

በጉበኤው የመጀመሪያ ቀን አህጉራዊ የሰላምና የጸጥታ ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚገልጽ ርእስ ቀርቦ ውይይት ተካሄዶበታል።

በተመሳሳይ የህብረቱ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት  "እ.አ.አ በ2020 የጦር መሳሪያ ድምጽ የማይሰማባትን አፍሪካ መፍጠር" በሚለው ፍኖተ ካርታ ትግበራ የተገኙ ለውጦች ላይም መሪዎቹ መክረዋል።

ጉባኤው ዛሬም ቀጥሎ ሲካሄድ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል።

በሊቢያ ሰላም ማስፈን፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ትምህርት፣ ሳይንስና ፈጠራ፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ፣ በጤና ጉዳዮች (ስነ ምግብ፣ ወባ፣ የጤና ፋይናንስ እንዲሁም ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ)፣ ጽንፈኝነት፣ አክራሪነትና የሙስና ወንጀል መከላከልና የጋራ የአየር ትራንስፖርት ገበያ መሪዎቹ የመከሩባቸው ጉዳዮች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም መሪዎቹ የተለያዩ ረቂቂ ሰነዶች ላይ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፤ በህብረቱ ኮሚሽኖች በተጓደሉ አባላት ምትክ ተተኪ አባላትንም መርጠዋል።

በጉባኤው ማጠናቀቂያ ስነ ስርዓት በቀድሞው የጋና ፕሬዚዳንት ክዋሚ ንኩሩማ ስም የተሰየመው አህጉራዊ የ2018 ምርጥ የሳይንስ እትም ሽልማት ተሰጥቷል።

የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት(ፋኦ) ዋና ዳይሬክተር ግራዚያኖ ዳ ሲልቫ የእውቅና የምስክር ወረቀት ከህብረቱ ተበርክቶላቸዋል።

ትናንት ህብረቱን ለቀጣይ አንድ ዓመት በሊቀ መንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፋታህ አልሲሲ የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በህብረቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተሳተፉ የአባል አገራት መሪዎች መልካም የስራ ዘመን ተመኝተዋል።

የአህጉሩን መሰረተ ልማት ለማዘመን እንደሚሰራ የገለጹት ሊቀ መንበሩ፤ በአህጉሩ ሰላምና ጸጥታን ለማስከበር እንዲሁም የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።

በተለይም የአባል አገራትን በማስተባበር የአጀንዳ 2063ን ከግብ ለማድረስ በትጋት መሰራት እንደሚገባ ነው ያወሱት።

ለወጣቶች የስራ እድልን ለመፍጠር መስራትም ወሳኝ በመሆኑ መሪዎች በዚህ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንድሰሩም ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም