የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስትሩ ከዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት ዋና ጸሃፊ ጋር ተወያዩ

959

አዲስ አበባ የካቲት 4/2011 የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ከዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት ዋና ጸሃፊ ሚስተር ሆሊን ዛኦ ጋር በኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ማሻሻያ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።

ሚኒስትሩ በኤሌክትሮኒክ አገልግሎቷ ከምትታወቀው ሀገረ እስቶኒያ ፕሬዝዳንት ክርስቲ ካልጁሊያድ ጋርም ተነጋግረዋል።

ሚኒሰትሩ ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓት የምትከተል አገር መሆኗን በመጥቀስ በተዋረዳዊ ተቋማዊ አሰራሩ በኤሌክትሮኒክ የመረጃ ስርዓቷን እሰከ ቀበሌዎች ድረስ በብሮድ ባንድ አገልግሎት ለማገናኘት እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።

የመረጃ ስርዓት ማዘመንም በአይሲቲ ዘርፉ ከዓለም አቀፉ የቴሌኮሚኒኬሽን ህብረት ድጋፍ እንደምትሻ ለዋና ጸሃፊው ገልጸውላቸዋል።

ከዋና ጸሃፊው ጋር በነበራቸው ውይይትም በጥቃቅንና አነስተኛ ቴክኖሎጂዎች፣ በአይሲቲ ዘርፍ የሴቶችን ድርሻ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች እንዲሁም ኢትዮጵያ ከወራት በኋላ ለምታስወነጭፈው ሳተላይት ፕሮጀክት ቴክኒካል ድጋፍ ላይም መወያያታቸውን አንስተዋል።

እንዲሁም ከሁለት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የቴሌኮም ኮንግረስ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለምታዘጋጅ ስለ ዝግጅቱም ምክክር አድርገዋል።

ዋና ጸሃፊው በተለይም በአፍሪካ በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ላይ ለመስራት ሰፊ እድል እንዳለ ገልጸው፤ ኢኮኖሚያዊ እድገትን በኢንፎርማሽን ቴሌኮሙኒኬሽን መምራት እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በሁሉም አገራት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን የገለጹት ሚስተር ሆውሊን፤ ተቋማቸው አፍሪካን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ እንደሚያድርግም አረጋግጠዋል።

በአፍሪካ አዳዲስ ቴክኖሊጂዎችን በማፍለቅ የአካባቢው ህዝብ በመረጃ መረብ እንዲተሳሰር የማድረግ አቅም ያላቸው ወጣቶች እንዳሉ ጠቅሰው፤ የግሉን ቴሌኮም ዘርፍ ለመደገፍም በቴሌኮም መሰረተ ልማት ላይ ከመንግስታት ጋር በትብብር እንሰራለን ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ከአውሮፓ አገሮች መካከል ሁሉንም መንግስታዊና የግል ተቋማት በኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ከዘረጋቸው እስቶኒያው ፕሬዝዳንት ጋርም ተወያይተዋል ሚኒስትሩ።

በውይይታቸው እስቶኒያ በመጭው ግንቦት ወር በምታስተናግደው ዓለም አቀፍ የኤሌክትሮኒክስ መንግስታዊ አገልግሎት ኮንፍረንስ በማየት ልምድ መውሰድ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መምከራቸውን አንስተዋል።

እስቶኒያ ከአውሮፓ አገሮች ሁሉ በበለጠ ሁሉንም ጉዳይ ዲጂታል ያደረገች መሆኗን ጠቅሰው፤ ከዲጂታል መታወቂያ ጀምሮ በዘርፉ ባላት ተሞክሮ ድጋፍ ለማድረግ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቷም አገራቸው መሰረታዊ አገልግሎቶችን ሁሉ ዲጂታል ማድረጓን ገልጸው፤ ይህን ልምዷን ከአፍሪከ ህብረት ጋር በተፈራረመችው የጋራ መግባቢያ ሰነድ መሰረት በዘርፉ ላይ ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።