የሰባት ቤት አገው የፈረስ ጉግስ ትርኢት በዓል በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋል...የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ

233

ባህር ዳር የካቲት 4/2011 የሰባት ቤት አገው የፈረስ ጉግስ ትርኢት በዓል ባህላዊ የቱሪዝም መስህብ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንዲመዘገብ የሁሉም አካላት ድጋፍ ያስፈልጋል ሲሉ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ተናገሩ።

የሰባት ቤት አገው የፈረስ ማህበር የፈረስ ጉግስ ትርኢት 79ኛ ዓመት ክብረ በዓል በእንጅባራ ከተማ ትናንት ተከብሯል።

በዓሉ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት የአዊ ብሔረሰብ ተወላጆች በፈረስ ተጓጉዘው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር ጠላትን ድል ያደረጉበትን ታሪክ ለመዘከር የሚከበር ነው።

ክብረ በዓሉ በተከበረበት ወቅት የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ እንዳሉት በዓሉ የአዊ ብሄረሰብ ተወላጆች ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮያውያን የጀግንነት ታሪክ ማስታወሻ ነው።

ይህነኑ ታሪካዊ በዓል በዩኔስኮ በማይዳሰስ የቱሪዝም መስህብነት እንዲመዘገብ የክልሉ መንግስት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

"በዓሉ ጎልቶ እንዲታወቅና በሃገር አቀፍ ደረጃ የላቀ እውቅና ኑሮት እንዲከበር ታሪኩን ከማስተዋወቅ ባለፈ በገንዘብና በእውቀት በማገዝ በዩኒስኮ እንዲመዘግ ማድረግ ይገባል" ብለዋል።

በዓሉ የጀግንነት ማስታወሻ ብቻ ሳይሆን የአብሮነትና ተሳስቦ የመኖር እሴቶችን አቅፎ የያዘ በመሆኑ ከብሔረሰብ አስተዳደሩ በተጨማሪ ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንዲስፋፋ በክልሉ መንግስት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የብሔረስብ አስተዳዳር ዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባይነሳኝ ዘሪሁን በበኩላቸው ማህበሩ የመቻቻልና በጋራ ተባብሮ የመኖር ባህልን አጠናክሮ ማስቀጠሉን ተናግረዋል።

በተለይም እንደሃገር አሁን የተጀመረው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የፈረስ ማህበሩ በሌሎች አካባቢዎች የሚስተዋሉ የግጭት ችግሮች በዞኑ እንዳይከሰት በትኩረትና በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት ።

በዓሉ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ታሪኩን በማስጠናትና መረጃዎችን በማሰባሰብ በባለቤትነት እየሰራ ይገኛል ያሉት ወይዘሮ ወርቅሰሙ፣ በአቅም ውስንነት በሚፈለገው ደረጃ መጓዝ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

በመሆኑም በዓሉ የመለው ኢትዮጵያውያን የድል ብርሃን በመሆኑ ተገቢውን ድጋፍና እገዛ በማድረግ እውቅናውን እንዲያገኝ ሁሉም ይድርሻውን ማገዝ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዓሉ በፈረስ ጉግስ ግልቢያ፣ በሙዚቃ ትርኢትና በሌሎች ባህላዊ ዝግጅቶች ትናንት ተከብሯል።

የሰባት ቤት አገው የፈረስ ማህበር ከተቋቋመ 79 ዓመት ያስመዘገበ ሲሆን በውስጡም 48 ሺህ በላይ የፈረሰኛ አባሎችን አቅፎ መያዙ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም