ለህወሓት 44ኛ ዓመት የወጣቶች የእግር ጉዞ ከደደቢት - መቀሌ እየተደረገ ነው

126

ሽሬ እንዳሥላሴ የካቲት 4/2011 የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) 44ኛው ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ወጣቶች ከደደቢት ወደ መቀሌ ከተማ የእግር ጉዞ እያደረጉ ነው።

''ክብር ለ44ኛው የትግልና የልማት ጉዞ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለው ጉዞ ለወጣቱ ትውልድ የቀድሞ ታጋዮችን አደራ ለማስረከብ መሆኑን የጉዞው አስተባባሪዎች ገልጸዋል።

አስተባባሪዎቹ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ተጓዦቹ የካቲት 11/2011 መቀሌ ላይ ለሚከበረው በዓል ጉዞውን እያደረጉ ያሉት ድርጅቱን የትጥቅ ትግል ከጀመረበት ቦታ ተነስተው ነው።

አራት ሴቶችን ጨምሮ 44 ወጣቶች የተካተቱበት ይሄ ቡድን 420 ኪሎ ሜትሮችን በማቋረጥ በዓሉ በሚከበርበት በመቀሌ ከተማ ጉዞውን እንደሚያጠናቅቅ የሚጠበቅ ሲሆን የትግሉ መስራቾችና ነባር ታጋዮች በደደቢት በረሃ ትላንት ሌሊት አሸኛኘት አድርገውለታል።

ከአስተባባሪዎቹ መካከል ወጣት ሃና ካህሳይ ''የቀድሞ የህወሓት ታጋዮች ደማቸውን አፍስስው ሰላምና ዴሞክራሲ በአገራችን እንዲሰፍን እንደታገሉ ሁሉ፤ ተተኪው ትውልድ ላቡን አፍስሶ ድህነትን ለማስወገድ መነቃቃትን ለመፍጠር ነው''ስትል የጉዞውን ዓላማ አብራርታለች።

"አገሪቱ ወደ አዲስ የብልፅግና ምዕራፍ ለማሸጋገር የጀግኖች አደራ ለማስታወስ እንዲረዳ ጭምር ነው" ብላለች።

የቀድሞ ታጋዮች ከደደቢት በረሃ ተነስተው ተልዕኳቸውን እንዳሳኩ ሁሉ፣ተተኪ ወጣቶችም የበለፀገች ኢትዮጵያን በመፍጠር አኩሪ ታሪክ ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቃለች።

ሌላው የጉዞው አስተባባሪ ወጣት ክብሮም ኪዳኑ "ጉዞው የትግሉ መስራቾች የጀመሩትን ትግል በማስቀጠል ከወጣቶች የሚጠበቀውን ተግባር በብቃት ለመወጣት ቃል የምንገባበት ይሆናል" ብሏል።

ከትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን የአስገደ ፅምብላ ወረዳ ወጣቶችን በመወከል የተሳተፈችው ወጣት ምፅላል አብርሃ  በበኩሏ የቀድሞ ታጋዮች በእግራቸው እልህ አስጨራሽ ትግልን በድል ተወጥተው ዓላማቸውን ማሳካታቸውን ትገልጻለች።

''ወጣቶች ረጅምና አድካሚ ጉዞ በማድረግ ልማቱን ለማስቀጠል ቃል የምንገባበት ታሪካዊ የእግር ጉዞው ጀምረናል'' ብላለች።

''የትግሉ ሰማዕታት አደራን በልማት ለመካስ ረጂሙን ጉዞ በእግር በመጓዝ ኃላፊነታችንን በብቃት ለመጣት ቆርጠን ተነስተናል” ያለው ደግሞ ከትግራይ ማእከላዊ ዞን የናእዴር አዴት ወጣቶችን የወከለው ወጣት ገብረእግዚአብሔር መንግሥት ነው።

የእግር ተጓዦቹ በሚደርሱባቸው ከተሞች አቀባበልና አሸኛኘት እየተደረገላቸው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም