የባኮ ብሔራዊ በቆሎ ምርምር ማዕከል ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ ነው

925

አዲስ አበባ የካቲት 4/2011  በሄክታር እስከ 100 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ሁለት ዓይነት የበቆሎ  ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ መሆኑን በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባኮ ብሔራዊ በቆሎ ምርምር ማዕከል አስታወቀ።

የማዕከሉ  ተልዕኮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ የበቆሎ ምርምር ፕሮጀክት ማስተባበርና የተሻሻሉ የበቆሎ ዝርዎችን ለአርሶ  አደሩ በማስተዋወቅ ምርታማነታቸው እንዲያድግ ማገዝ ነው።

እስካሁንም ከ20 በላይ ድቃይና ድቃይ ያልሆኑ የበቆሎ ዝርያዎችን በመልቀቅ አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ማድረጋቸውን የማዕከሉ ስራ አስኪያጅና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር ብርሃኑ ታደሰ ኢዜአ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ በ1990ዎቹ የበቆሎ ምርታማነት በሄክታር 12 ኩንታል የነበረው በተለቀቁት  የተሻሻሉ ዝርያዎች  በአማካኝ ከሶስት እጥፍ በላይ  ማሳደግ ተችሏል።

ዶክተር ብርሃኑ ” በቅርቡ የተለቀቁት ቢኤች 546 እና ቢኤች 547 የተባሉት ሁለት የበቆሎ ዝርያዎች በአሁኑ ጊዜ ለአርሶ አደሩ በስፋት በማስተዋወቅ ላይ እንገኛለን “ብለዋል።

ዝርያዎቹ ዘንድሮ በአርሶ አደሩ ማሳ በተደረገው የሙከራ ስራ በሔክታር እስከ 100 ኩንታል ማስገኘታቸውን ጠቁመው በሽታና የተፈጥሮ ችግርን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት እንደሚሰጡ መረጋገጡን አስረድተዋል

ማዕከሉ የተሻሻሉትን መነሻ ዝርያዎችን በመልቀቅ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ የሚደረገው በኢትዮጵያና በየክልሎቹ ምርጥ ዘር  ድርጅቶች እንዲሁም በግለሰቦች አማኝነት በማባዛት ነው።

ሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የበቆሎ ሰብል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ያመለከቱት ዶክተር ብርሃኑ በቀጣይ ዝርያዎችን ማስተዋወቁን በስፋት በመቀጠል ሁሉም የሀገሪቱ  በቆሎ አምራች ገበሬዎችን ምርታማነት ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር  እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ግብርና ምርምር የባኮ ማዕከል ስራ አስኪያጅ ተወካይና የአዝርዕት ተመራማሪ አቶ አዳነ አረጋ በበኩላቸው ማዕከሉ  የበቆሎ ዝርያዎችን እያባዙ ለክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅትና ለግለሰቦች በማድረስ እነሱ መልሰው በማራባት ለአርሶ አደሩ እንደሚያሰራጩ ተናግረዋል።

እስከ አሁን የወጡት የበቆሎ ዝርያዎች  ችግርን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት እንደሚሰጡ  በተግባር ማረጋገጣቸውን አመልክተው  ውጤታማነትን ለማጎልበት ከብሔራዊ የምርምር ማዕከሉ ጋር ተቀራርበው በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አቶ በየነ አበበ በብሐራዊ የምርምር ማዕከሉ የሰብል ምርምር የስራ ሂደት ተጠሪ ሲሆኑ የተለቀቁ የበቆሎ ዝርያዎችን ለማስተዋወቅ በምዕራብ ሸዋና በምስራቅ ወለጋ ዞኖች ለናሙና በተመረጡ 41የአርሶ አደሮች ማሳ ባደረጉት ሙከራ ተቀባይነቱ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባለፈው የምርት ዘመን ሙከራ በተካሄደባቸው ማሳዎች እስከ 108 ኩንታል የበቆሎ ምርት ያገኙ አርሶ አደሮች እንዳሉ ጠቁመው በውጤቱ የብዙዎችን ትኩረት በመሳቡ ለማስፋፋት እየሰሩ መሆናቸውን አመልክዋል።

በምዕራብ ሸዋ ዞን  ኢሉ ገላን ወረዳ የሲባ ቢቼ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ደርቤ ተርፋ በብሔራዊ የምርምር ማዕከሉ ማሳቸው ለናሙናነት ከተመረጡት አርሶ አደሮች መካከል አንዱ ናቸው።

ከማዕከሉ ምርጥ የበቆሎ ዘር፣ ማዳበሪያ አቅርቦትና የተመራማሪዎች የቅርብ እገዛ  ተደርጎላቸው ባለፈው የምርት ወቅት ባካሄዱት ልማት በሄክታር 80 ኩንታል  ማግኘታቸውን አርሶ አደር ደርቤ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ይህም ከአካባቢው ዝርያ የተሻለ ውጤት መሆኑና ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች አይተው ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላቸው  ገልጸዋል።

በግብርና ስራ የተሰማሩ ባለሀብትና የአምቦ ከተማ ነዋሪ  አቶ ጋዲሳ ጎበና የባኮ በቆሎ ብሔራዊ ምርምር ፕሮጀክት ከሚያፈልቃቸው መስራች የበቆሎ ዝርያዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አቶ ጋዲሳ እንዳሉት ከማዕከሉ የሚያገኙትን ዘር በማባዛት የሚያሰራጩ ሲሆን ዝርያዎቹ የላቀ ውጤት በማምጣታቸው በተለይ በባኮ አካባቢ ያለሙ አርሶ አደሮች እስከ 90 ኩንታል በሄክታር እያገኙ ነው፤ እሳቸውም የሚያለሙበት ቦታ አነስተኛ ቢሆንም ውጤታማ ናቸው።

የባኮ ብሔራዊ በቆሎ ምርምር  ማዕከል ተመራማሪዎችና የአስተዳደር ሰራተኞችን ጨምሮ 90 የሰው ኃይል ይዞ በዓመት ለዘር ማምረቻና ለምርምር 30  ሄክታር መሬት ይጠቀማል።