የደካሱስ ጄሶና ኖራ ማምረቻ ፋብሪካ ሠራተኞች ላለፉት አምስት ዓመታት የጥቅማ ጥቅም መብታችንን አላከበረልንም-ሠራተኞች

54

አምቦ የካቲት 4/2011 የደካሱስ ጄሶና ኖራ ማምረቻ ፋብሪካ ሠራተኞች ላለፉት አምስት ዓመታት ከድርጅቱ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅማ ጥቅም እንዳላገኙ ገለጹ።

ፋብሪካው የሠራተኞቹን ጥያቄ  ለመመለስ ተዘጋጅቻለሁ ብሏል።

ከሠራተኞቹ አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ከድርጅቱ ሊጠበቅላቸው የሚገባ ጥቅማ ጥቅም እየተከበረላቸው አይደለም።

ቅሬታቸውን ከገለጹት ሠራተኞች  መካከል በፋብሪካው በጥበቃ ሥራ ለ11 ዓመታት ያገለገሉት አቶ ጥላሁን ለማ አንዱ ናቸው።ለሥራቸው አስፈላጊ የሆኑ ካፖርትና ብርድ ልብስ ላለፉት ዓመታት እንዳላገኙ ይናገራሉ።

በዚህም ምክንያት ለብርድ እየተጋለጡ በተደጋጋሚ ጊዜ ለህክምና ወጪ መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

ሌላው ሠራተኛ አቶ ጉደታ ዲንቃ በበኩላቸው በኢንዱስትሪው ሲቀጠሩ በገቡት ውል መሠረት ማግኘት የሚገባቸውን ልብስና ጫማ አላገኘሁም ይላሉ።

በየወሩ ለወተት ተብሎ የሚሰጣቸው 250 ብር እንደተቋረጠባቸውም አቶ ጉደታ አመልክተዋል።  

"የምንሰራው ማሽን ላይ እንደመሆኑ መጠን የእጅ ጓንት ያስፈልገናል፣ በተደጋጋሚ ጊዜ ብንጠይቅም ፋብሪካው ሊያሟላልን አልቻለም" ያሉት ደግሞ አቶ ንጉሴ ሂርጳ የተባሉ ሠራተኛ ናቸው።

ስጋት ውስጥ ሆነው ሥራቸውን ለማከናወን መገደዳቸውን የሚናገሩት አቶ ንጉሴ፣ችግሩን በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም ምላሽ አላገኘሁም ብለዋል።

የፋብሪካው  ባለቤት አቶ ካሳወይ አዲሱ የሠራተኞች ቅሬታ ተገቢና ትክክለኛ መሆኑን ያምናሉ።የሠራተኛው ብዛትና ወጪ ባለመመጣጠኑ ጥቅማ ጥቅማቸውን አለመሟላቱን አልካዱም።

በዚህም ምክንያት ፋብሪካው የነበሩትን 110 ሠራተኞች ወደ 30 መቀነሳቸውን ተናግረዋል።

በሥራ ላይ ለሚገኙት ሠራተኞችም የቀረባቸውን ጥቅማጥቅም ወደ ገንዘብ ለውጠው ለመክፈል መስማማታቸውን ገልጸዋል።

የደካሱስ ጄሶና ኖራ ማምረቻ ፋብሪካ  በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ልዩ ቦታው ሰንቀሌ ተብሎ በሚጠራ ሥፍራ  ይገኛል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም