በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች በማሸነፍ ጉዟቸው ቀጥለዋል

71

አዲስ አበባ የካቲት 4/2011 በ2011 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አምስተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል።

የፕሪሚየር ሊጉ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሄደዋል።

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፌደራል ፖሊስን 37 ለ 29፣ ድሬዳዋ ላይ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 29 ለ 19 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

ውጤቱን ተከትሎም ቂርቆስና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በሊጉ አምስተኛ ተከታታይ ድላቸውን በማስመዝገብ በአሸናፊነት ግስጋሴያቸው ቀጥለዋል።

የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በሊጉ ብርቱ ፉክክር በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ሌላ ጨዋታ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከሜዳው ውጭ መከላከያን 23 ለ 21 አሸንፏል።

ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ፌደራል ማረሚያ ቤቶችና ከምባታ ዱራሜ ያደረጉት ጨዋታ 23 ለ 23 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከፍተኛ ሃይል የተቀላቀለበትና ፍትጊያ የበዛበት ጨዋታ ነበር።

በጨዋታው ፌዴራል ማረሚያ ተጋጣሚውን 30 ሴኮንድ እስኪቀረው 23 ለ 22 እየመራ የነበረ ቢሆንም ከምባታ ዱራሜ 30 ሴኮንድ ሲቀረው ፍጹም ቅጣት ምት አግኝቶ ግብ በማስቆጠር ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ባለፈው ሳምንት መቐለ ላይ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ጋር ባደረገው ጨዋታ 25 ለ 25 በሆነ የአቻ ውጤት ማጠናቀቁ ይታወሳል።

የፌደራል ማረሚያ ቤቶችና ከምባታ ዱራሜ አሰልጣኞች ዳኞች የሚወስኑዋቸውን ውሳኔዎች በመቃወም በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ዳኞች መቀመጫ በመሄድ ሲያደርጉት የነበረው ተግባር ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ የነበረና ሊታረም የሚገባው ነው።

ትናንት ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ጎንደር ከተማን 23 ለ 22 በማሸነፍ በሊጉ ከአራት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ የመጀመሪያ ድሉን ያስመዘገበ ሲሆን፤ በአንጻሩ ጎንደር ከተማ በሊጉ አምስተኛ ተከታታይ ሽንፈቱን አስተናግዷል።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ 10 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ መቐለ ሰብዓ እንደርታ በዘጠኝ ነጥብ ሶስተኛ ሆኖ ይከተላል።

አዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ጎንደር ከተማ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 10ኛ ደረጃ ይዟል።

በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 10 ቡድኖች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።                                 

በሌላ በኩል የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም የተጀመረውና ስድስት ቡድኖች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ  በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ሁለት ጨዋታዎች ተካሄደዋል።

በዚሁ መሰረት ከትናንት በስቲያ ወልቂጤ ላይ ወልቂጤ ከተማ ቢጂ አይ ኢትዮጵያን 74 ለ 49 አሸንፏል።

ትናንት ወልቂጤ ላይ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን ቢጂ አይ ኢትዮጵያን 85 ለ 37  ማሸነፍ ችሏል።

የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ሁሉንም ክለቦች በአንድ ምድብ በማካተት በዙር ያካሄድ የነበረውን የውድድር ፎርማት በ2011 ዓ.ም በመቀየር በሁለቱም ጾታዎች የሚሳተፉት ቡድኖች በሁለት ምድብ ተከፍለው በዙር ጨዋታቸውን እንዲያደርጉ የሚያስችል ፎርማት አዘጋጅቷል።

በዚሁ መሰረት በሴቶች በምድብ ”ሀ ”ወልቂጤ ከተማ፣ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይንና ቢጂአይ ኢትዮጵያ የተደለደሉ ሲሆን በምደብ ”ለ ” ደግሞ ጎንደር ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተደልድለዋል።

በውድድሩ ፎርማት መሰረት በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በምድብ አንድ ላይ የተደለደሉት ሶስቱ ክለቦች ወደ ወልቂጤ በማቅናት ለሶስት ተከታታይ ቀናት እርስ በእርሳቸው ተጫውተዋል።

የካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም በሊጉ መክፈቻ ጨዋታ የአምናው የሊጉ አሸናፊ ወልቂጤ ከተማ አማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይንን 66 ለ 65 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን በድል መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ወንዶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል።

በተጨማሪም በሰባተኛው ሳምንት የሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ አንድ ጨዋታ ሙገር ሲሚንቶ በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽን 3 ለ 0 አሸንፏል።

በአፍሪካ የዞን 5 የቮሊቦል የክለቦች ውድድርና በተደራራቢ ጨዋታዎች ምክንያት ለተወሰኑ ቡድኖች የእረፍት ጊዜ መስጠት ስላስፈለገ በሳምንቱ አንድ ጨዋታ ብቻ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።

በሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ስምንት ቡድኖች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም